ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው
ሐረር፤ መጋቢት 16 ቀን 2014(ኢዜአ) በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና የደረሱ ተፅእኖዎችን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሐረር ከተማ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የ2014 የበጀት ዓመት ሁለተኛው የህብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር ፎረም ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሀረላ አብዱላሂ እንደተናገሩት፤ ኮሮናና ሌሎች ወረርሽኞችን በተቀናጀ መልኩ መምራት ያስፈልጋል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃና በክልሎች የወረርሽኝ ቁጥጥር ማዕከላትን ወደ ስራ በማስገባት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ በተቀመጠለት የልኬት መስፈርት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ነው ያመላከቱት፡፡
ባለፉት ዓመታትም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች የጤና ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቁመው፤ በእነዚህ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ወገኖች የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና የደረሱ ተፅእኖዎችን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም የማስተባበሪያ ማዕከላት በማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ በበኩላቸው፤ ወረርሽኞችን ለመከላከል በሀገር አቀፍና በሁሉም ክልሎች የድንገተኛ ማስተባበሪያ ማዕከላት መቋቋማቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪ በተያዘው ዓመት በተመረጡ አምስት ዞኖች ማዕከላት መቋቋሙንና ምላሽ የመስጠት ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከጤና ሚኒስትር፣ ከክልሎችና አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሀገሪቱ በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ከ2008 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በሀገሪቱ 19 ሺህ 844 የኮሌራ ህሙማን መመዝገባቸውንና በዚህም ምክንያት የ327 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውሰው፤ ሆኖም በተደራጀ አግባብ በተከናወኑ ተግባራት በአሁኑ ወቅት በሽታውን መቆጣጠር መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ፎረሙ የተከናወኑ ተግባራት የሚገመገምበት፣ ያጋጠሙ ችግሮችን የሚፈተሹበትና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ ተግባራትና የተወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ወሳኝ ሚና የነበራቸው ቢሆንም አሁንም ያልተሻገርናቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉ ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኢብሳ ሙሳ ናቸው፡፡
የእናቶችና የጨቅላ ህፃናትን ሞት፣ የኤች. አይ. ቪ ኤድስ ስርጭት፣ኮሮና እና የሌሎችም በሽታዎች ስርጭትን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አንፃር አሁንም ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም በየደረጃው የሚገኘው አመራር በእቅድ መመራትና በወቅቱ መገምገም እንዲሁም ላጋጠሙ ችግሮች አስፈላጊ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ነው ያመላከቱት፡፡
ለሶስት ቀናት በሚቆየው ሀገር አቀፍ ፎረሙ ላይ የፌደራልና የሁሉም ክልሎች የጤና ዘርፍ አመራሮች እንዲሁም ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ነው።