ቀጥታ፡

በአሶሳ የጸጥታ ስጋትና የመሬት ወረራን ለማስቀረት ዲጂታል የነዋሪነት መታወቂያ መሰጠት ተጀመረ

አሶሳ ፤ መጋቢት 15 / 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የጸጥታ ስጋትንና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ዲጂታል የነዋሪነት መታወቂያ ዛሬ መሰጠት ተጀመረ፡፡

መታወቂያው መሰጠት በተጀመረበት ሥነሥርዓት ላይ  የከተማ አስተዳደሩ ተወካይ አቶ ያዕቆብ ሙስጣፋ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም በየቀበሌው ሲሰጥ የነበረው የመታወቂያ ደብተር በከተማው በሚገኙ ኮምፒዩተር ቤቶች ተመሳስሎ ሲዘጋጅ ነበር፡፡

ይህም ከተለያዩ ክልሎች እና ከአጎራባች ሀገር  ከተፈናቃዮች እና ስደተኞች ጋር ተቀላቅለው በመግባት የህብረሰተቡን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ሲጠቀሙበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በከተማው ነዋሪ ያልሆኑ ግለሰቦች ተመሳስሎ የተሠራውን መታወቂያ በመያዝ በግል እና በማህበር ተደራጅተው በህገወጥ መንገድ የመኖሪያ እና የኢንቨስትመንት መሬት ሲወስዱ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ይህም በከተማው ውስን የመሬት ሃብት ያለአግባብ ጥቂት ህገ-ወጥ ግለሰቦችን እንዲወረር ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ዲጂታሉ መታወቂያ ለማውጣት እና በተያያዥ ጉዳዮች አለመሟላት ጨምሮ የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግር እንደሚያስቀር አቶ ያዕቆብ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ጠቅላይ አቃቢ ህግ የጥናት እና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አሰፋ ፤በከተማው ቀበሌዎች የነዋሪነት መታወቂያ ለማውጣት አለአግባብ  እስከ ሶስት ሺ ብር እንደሚከፈል ገልጸዋል፡፡

በዚህም ግለሰቦች ከአዲስ አበባ አሶሳን አቋርጠው ወደ ሱዳን በመጓዝ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲስፋፋ አድርጓል ብለዋል፡፡

አዲሱ መታወቂያ እንኚህን ችግሮች እንዲያስወግድ ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

መታወቂያው መሰጠት ሲጀመር ከነበሩት ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ፋጡማ መሃመድ በሰጡት አስተያየት፤ ዲጂታል መታወቂያው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ግለሰቦች ኪስ የሚገባውን የመታወቂያ ክፍያ ያስቀራል ብለዋል፡፡

በከተማው ህብረተሰብ ላይ አደጋ ለመጣል የሚመጡ የጥፋት ሃይሎችንም የጸጥታ አስከባሪ አካላት በቀላሉ እንዲቆጣጠሩ እንደሚያደርግ እምነት አለኝ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በየኬላዎች የዲጂታል መታወቂያ መቆጣጠሪያ ስለሚኖር የፀጥታ ሃይሉ ትክክለኛ ማንነትን በሙባይል ስልክ መተግባሪያ ጭምር ለይቶ ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም