ቀጥታ፡

የምግብ ሰብል ምርታማነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ግብርናው በቴክኖሎጂ ሊደገፍ ይገባል

መጋቢት 14/2014 (ኢዜአ)  የምግብ ሰብል ምርታማነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ግብርናው በቴክኖሎጂ ሊደገፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ በቂ የሚለማ መሬት፣ ወቅቱን የጠበቀ ተመጣጣኝ ዝናብ እና በርካታ ምርታማ ኃይል ቢኖራትም  በምግብ ራሷን መቻል አቅቷት በርካታ ዘመናትን ተሻግራ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡

ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ፍላጎት ለማሟላት ዛሬም በርካታ የሰብል ምርቶችን በግዥና በእርዳታ ከውጭ ታስገባለች፡፡

ነገር ግን ካለው ፍላጎት አንጻር በግዥም ሆነ በእርዳታ የሚገኘውን እህል ለህብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ ማዳረስ ባለመቻሉ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ዜጎች ለምግብ እጥረት ተዳርገዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ተመራማሪ ዶክተር ታደሰ ኩማ ይህንኑ ችግር ለመፍታት በእውቀት የሚመራና በፋይናንስ ራሱን የቻለ ጠንካራ ተቋም መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በሰው ኃይል የተጠናከረ፣ የፋይናንስ አቅም ያለው የግብርና ግብዓቶችን በተጠና መንገድ ለአርሶ አደሩ የሚያቀርብ ተቋም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ እስከታችኛው መዋቅር ያሉ አደረጃጀቶችም ተናበው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በምግብ ምርት ራሳቸውን ችለው ወደ ውጭ የሚልኩ አገራት ችግሩን የተሻገሩት በእውቀት የሚመራ ጠንካራ የግብርና ተቋም መገንባት በመቻላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር  የግብርና ምርት ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ እጥረቱን ለመቅረፍ ምርትና ማርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን በስፋት ማምረት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ለአርሶ አደሮች መሰረታዊ የግብርና እውቀት በማስጨበጥ ዘርፉን በእውቀት መምራትና የግብርና መካናይዜሽንን ማስፋፋት ለምርትና ምርታማነት መጨመር ቁልፍ ዘዴ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተለይ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በሄክታር የሚገኘው ምርት እንዲጨምር መሥራት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡

የምግብ ሰብል ምርታማነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ግብርናው በቴክኖሎጂ ሊደገፍ እንደሚገባ የተናገሩት ዶክተር ታደሰ፤ በዘርፉ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ በቀላሉ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ መሆን እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የሚሰሩ ምርምሮችም በአርሶ አደሩ ተጨባጭ ችግር ላይ መመርኮዝ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ በተለይም ባለሃብቶች በግብርናው ሴክተር በስፋት እንዲሰማሩ የሚያደርግ አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

በቆላማ አካባቢዎች የተጀመረው ስንዴን  በመስኖ የማምረት ሥራም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም