የአዲስ አበባ ከተማን ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል የስማርት ከተማ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማን ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል የስማርት ከተማ ፍኖተ ካርታ በመዘጋጀት ላይ ነው
መጋቢት 14/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማን ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችል የስማርት ከተማ ፍኖተ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ፍኖተ ካርታውን የሚያዘጋጁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክ ሙያ፣ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን ነው ተብሏል፡፡
በዛሬው እለትም ለዚሁ ስራ ግብዓት ማሰባሰብ የሚያስችልና የተለያዩ ባለድርሻ ተቋማት የተሳተፉበት ወርክ-ሾፕ ተካሂዷል፡፡
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን ሃብቱ በዚህን ወቅት ፍኖተ ካርታው የአዲስ አበባን ተጨባጭ ጥንካሬዎችና ክፍተቶችን መሠረት በማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም የተለያዩ አገልግሎቶች በተቀናጀ መንገድ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ለማድረግ የሚያስችሉ ስልቶች መነደፋቸውን ተናግረዋል።
ትምህርት፣ ጤና፣ የትራንስፖርት፣ ግብይት፣ የፋይናንስ እንቅስቃሴ፣ የደህንነትና ጥበቃ፣ የመሳሰሉ ዘርፎችን ከወዲሁ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
ፍኖተ ካርታው አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹና ተስማሚ እንደሚያደርጋት ጠቅሰው፤ ለማዘጋጀት የታቀደው ፍኖተ ካርታም ከ15 እስከ 20 በሚሆኑ ዓመታት አገልግሎት እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም ፍኖተ ካርታውን በሚመለከት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አብርሃም ደበበ በበኩላቸው አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የፍኖተ ካርታው ዝግጅት መዲናዋን ዘመናዊ ለማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡