ቀጥታ፡

መንግስት ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎችን በመቃወም ያልተቋረጠ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ መንግስት ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ በመቃወም ያልተቋረጠ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በፖለቲካ፣ ምጣኔ ኃብትና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ረገድ በሳምንቱ የተከናወኑ ተግባራት ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

በሳምንቱ በአሜሪካ ኮንግረንስ ኤች አር 6600 እና በአሜሪካ ሴኔት ኤስ 3199 ረቂቅ ሕጎች ይዘትና የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማብራሪያ መስጠታቸውን አውስተዋል።

ሕጎቹ ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ፣ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ በኩል እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን የሚሸረሽሩ ውሳኔዎች እንደሚሆኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የምጣኔ ሃብት፣ የፖለቲካና ደህንነት ጥገኛ የሚያደርጉ በመሆኑ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሊቃወሙት እንደሚገባ አብራርተውላቸዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በኢትዮጵያ ላይ የተደረገውን ጫና #NO MORE ወይም "በቃ" ብለው በታገሉት ልክ ይህም የጫናው አካል በመሆኑ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ በአደረጃጀት እንዲታገሉ አስገንዝበዋል።

ሕጎቹ ከጸደቁ የአሜሪካንና የኢትዮጵያን ታሪካዊ ግንኙነት እንደሚጎዳ፣ የኢትዮጵያን መንግስት ደካማና የሚጠመዘዝ እንዲሆን የሚፈቅድ በመሆኑ ከኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች ጋር ውይይቶችን እንዲያካሂዱ ተጠይቋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አካታች አገራዊ ምክክር ለማድረግ እየሰራች መሆኑን በማስታወስ፤ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ በአሜሪካ ኮንግረስ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ወገኖች እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ተደርጓል ብለዋል ቃል አቀባዩ።

በሴኔት ላይ ያለው ኤስ 3199 ቢል ትላንት ቀርቦ ሴኔቱ ለአንድ ሳምንት ወደ ፊት መውሰዱን ጠቁመው በኮንግረሱ የሚገኘው ኤች አር 6600 ደግሞ በቀጣይ ሳምንት እንደሚታይና እስከዚያው ተቃውሞዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ዳያስፖራው እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እዳለ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት ሕጎቹን በመቃወም በኩል ያልተቋረጠ ጥረት እያደረገ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በአመዛኙ ዳያስፖራው የአሜሪካ አገር ነዋሪ እንደመሆኑ መጠን ተሰሚነቱም በዚያው ልክ ስለሆነ ይህም ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ በአሜሪካ ወዳጆችና በጋራ ወዳጆች በኩልም ሕጎቹ ጎጂ መሆናቸውን እንዲያስረዱ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጨምረዋል።

ሰሞኑን ኢትዮጵያ የነበሩት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ዴቪድ ስታተርፊልድ ከአቶ ደመቀ ጋር በነበራቸው ውይይት ጉዳዩ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ አስተዳደር በኩል የሚፈለግ እንዳልሆነ ለመገንዘብ ተችሏል ሲሉም አክለዋል።

''የአሜሪካ አስተዳደር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ዳግም ግንኙነቱን ለማጠናከር ጥረት እያደረገ ነው ያለው" በማለት ጥረቱ ገንቢ መሆኑን ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከወራት በፊት ለገና እና ጥምቀት በዓል ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ታላቁ "ጉዞ ወደ አገር ቤት" በሚል እንቅስቃሴ የተሳካ ተግባር ማከናወናቸውን አውስተዋል።

በተመሳሳይ "ከኢድ-አልፈጥር እስከ ኢድ አል-አድሃ" በሚል ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለማሳተፍ  ለመጪው የኢድ በዓል ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል።

በኢንቨስትመንት፣ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሳምንቱ የተከናወኑ ተግባራት ላይ ቃል- አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ማብራሪያ ሰጥተዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም