የፈረንሳይ አቦ - 05 የ1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ላለፉት ሁለት ዓመታት ባለመጠናቀቁ ነዋሪዎችን ለችግር ዳርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የፈረንሳይ አቦ - 05 የ1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ ላለፉት ሁለት ዓመታት ባለመጠናቀቁ ነዋሪዎችን ለችግር ዳርጓል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15/ 2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ የፈረንሳይ አቦ - 05 የ1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ላለፉት ሁለት ዓመታት ባለመጠናቀቁ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ።
የመንገዱ ግንባታ በጅምር በመቅረቱ በክረምት ለጎርፍ፣ በበጋ ደግሞ ለአቧራ እየዳረጋቸው በመሆኑ ለእንቅስቃሴ አስቸጋሪ ሆኖብናል፤ ለበሽታም እየዳረገን ነው ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
የኢዜአ ሪፖርተር በአካባቢው ባደረገው ቅኝትም መንገዱ ተጀምሮ በመቋረጡ በአካባቢው ውሃ በማቆር የቆሻሻ ማጠራቀሚያና የመጥፎ ሽታ ምክንያት መሆኑን አረጋግጧል።
ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል መምህር ሀብታሙ ከበደ፤ የመንገዱ ግንባታ መዘግየት አካባቢውን ለመግቢያና መውጫ አስቸጋሪ ከማድረግ ባለፈ በተከማቸው ቆሻሻ ለበሽታ በመዳረግ የጤና ጠንቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የተለያዩ ምክንያቶች እየተሰጡን ለዓመታት መንገዱ ሳይጠናቀቅ በመቆየቱ በክረምትም ይሁን በበጋ የችግር መንስኤ ሆኖ ቀጥሏል ያሉት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ኃይሉ ዶላ ናቸው።
በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪ የጤና ችግርና የመውጫ መግቢያ እንከን የሆነው የ1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ በአፋጣኝ ይጠናቀቅልን ሲሉ ጠይቀዋል።
መምህር ሀብታሙ ከበደ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በክረምት ወቅት፣ነብሰ ጡሮች የወሊድ ጊዜ ሲደርስና ሰዎች በሞት ሲለዩ መንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ገልፀው አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በርካታ ጊዜያት ሃላፊዎቹ ቢጠየቁም መንገዱ በወቅቱ ተጠናቆ ወደ ሰራ ያልገባበት ምክንያት ከመደርደር እና ዘንድሮ ያልቃል ከማለት ውጪ በተግባር የተለወጠ ነገር አለማየታቸው የገለፁት ደሞ አቶ ኃይሉ ዶላ የጠባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው፡፡
መምህር ተክለማርያም ክብረት እና ወይዘሮ መሰረት ቤክሲሳ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪዎችም በመንገዱ መቆፈር ምክንያት ወደ መኖሪያ ቤታቸው ጎርፍ በመግባቱ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም አሁንም የዝናብ ወቅት በመሆኑ ለሌላ ችግር እንዳንዳረግ መንገዱ አፋጣኝ መፍትሔ ይፈለግለት ሲሉ ጠይቀዋል።
የመንገዱን ግንባታ በወራት ውስጥ ማጠናቀቅ እየተቻለ ለዓመታት ማጓተት የአካባቢውን ነዋሪ ለችግር ከመዳረጉ ባለፈ መንግስትን ላልተገባ ወጪ የሚዳርግ በመሆኑ ግንባታው በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እያሱ ሰለሞን፤ ከ1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትሩ የመንገድ ግንባታ 800 ሜትሩን የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት የማልበስ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
የመንገዱ ግንባታ ከተጀመረ ሁለት ዓመት እንደሆነው ገልጸው፤ የድልድይ ግንባታው የዲዛይን ማስተካከያ እየተደረገለት በመሆኑ ቀሪ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ብሎ የተሰራውና አማካሪ ድርጅቱ ያቀረበው ዲዛይን ጋር አጣጥሞ መሥራት ስላስፈለገ የዲዛይን ክለሳ ማስፈለጉንም አስረድተዋል።
በተቻለ ፍጥነት የዲዛይኑ ሥራ ተጠናቆ የግንባታ ሥራው ይጀመራል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የዲዛይን ሥራው ተጠናቆ የመንገዱ ግንባታ ሥራ የሚጀመር ሲሆን፤ በክረምቱ ዝናብ ኀብረተሰቡ ለአደጋ እንዳይጋለጥ ጊዜያዊ የመፍትሔ ሥራዎችን ክትትል በማድረግ ይከናወናልም ብለዋል።
የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችንና ሌሎች ንብረቶችን ከቆሻሻም ሆነ ከሌሎች ጉዳቶች የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ግንባታው የሚከናወነው የፈረንሳይ አቦ - 05 የአስፋልት መንገድ ግንባታ ጠቅላላ ርዝመቱ 1 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ሲሆን ስፋቱ
ደግሞ 15 ሜትር ነው።