ቀጥታ፡

አዲስ የተሾሙት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ልምድ ያካበቱና የተቋሙን ስኬት የማስቀጠል ብቃት እንዳላቸው የታመነባቸው ናቸው

መጋቢት 15/ 2014(ኢዜአ) አዲስ የተሾሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ልምድ ያካበቱና የተቋሙን ስኬት የማስቀጠል ብቃት እንዳላቸው የታመነባቸው መሆናቸውን የአየር መንገዱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በጤና እክል ምክንያት በፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ አቶ መስፍን ጣሰው ለአየር መንገዱ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል።

አየር መንገዱ አዲስ ስለ ተሾሙት ሥራ አስፈጻሚና የቦርድ አመራሮችን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የአየር መንገዱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ በዚሁ ወቅት ቦርዱ ከመንግስትና ከሚመለከተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመነጋገር ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሾም አድርጓል ብለዋል።

በዚህም በአየር መንገዱ ከ38 ዓመታት በላይ በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ያገለገሉት አቶ መስፍን ጣሰው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ መስፍን ጣሰው  ከአሥር ዓመታት በላይ በአየር መንገዱ ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር በመሆን በተሻለ የአመራር ብቃት ማገልገላቸውንም ነው ያነሱት፡፡

በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ ድርሻ ባለው የቶጎ አስካይ አየር መንገድ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን የቦርዱን ውሳኔ በመቀበል አገራቸውን ለማገልገል ፍቃደኝነታቸውን ስለመግለጻቸውም አቶ ግርማ ዋቄ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አየር መንገዱ የቦርድ አባላቱን በአዲስ መልክ ያዋቀረ ሲሆን፤ አቶ ግርማ ዋቄ የቦርድ ሰብሳቢ እንዲሁም አቶ ተክለወልድ አጥናፉ፣ አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ፣አቶ ታደሰ ጥላሁን፣ አቶ ረታ መላኩ እና አቶ ዓለማየሁ አሰፋ የቦርድ አባል ሆነው መሾማቸውም ተገልጿል፡፡

አቶ መስፍን ጣሰው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሥራውን ሙሉ ለሙሉ እስከሚረከቡ ድረስ አቶ ቡሴራ አወል አየር መንገዱን በጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንደሚመሩም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም