ቀጥታ፡

የፊልም ፖሊሲ ቢዘጋጅም ባለመተግበሩ የዘርፉን ዕድገት ወደ ኋላ እየጎተተው ነው ተባለ

መጋቢት 15 /2014(ኢዜአ) የፊልም ፖሊሲ ቢዘጋጅም ባለመተግበሩ የዘርፉን ዕድገት ወደ ኋላ እየጎተተው መሆኑን የኢትዮጵያ የፊልም ሰሪዎች ማኅበር ገለጸ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በበኩሉ ለፖሊሲው ማስፈፀሚያ የሚሆኑ የሕግ ማዕቀፎችና ስትራቴጂዎች ይዘጋጃሉ ብሏል።

የኢትዮጵያ የፊልም ታሪክ የጀመረው በ1889 ዓ.ም በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት "ቤንሀር" የተሰኘ የኢየሱስ ክርስቶስን ገድል የሚያሣይ ኃይማኖታዊ ዘጋቢ ፊልም ለመጀመሪያ ጊዜ ከታየ በኋላ መሆኑ ይነገራል።

ከ1909 ዓ.ም በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲኒማ ቤቶች በተለያዩ ቦታዎች  መከፈት እንደጀመሩም በታሪክ የተሰነደ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ድሬዳዋ፣ ሀረር፣ ጎንደር፣ አስመራ እና ደብረማርቆስ ከተሞች ተጠቃሽ ናቸው።

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ደግሞ በኢትዮጵያ ፊልሞች ጊዜው የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በብዛት እየተሰሩ መውጣት ጀምረዋል።

ይህንኑ ጅምር ጥረት የበለጠ ለማጠናከር በ2010 ዓ.ም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች፣ ከኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲዩሰሮችና ከአላቲኖስ የፊልም ሠሪዎች ማኅበር ጋር በመሆን  የፊልም ፖሊሲ ቀርጿል።

ሆኖም የወጣው ፖሊሲ ባለመተግበሩ በዘርፍ ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር ገልጿል።

የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ የፊልም ባለሙያ ወይዘሮ አርሴማ ወርቁ፣ የመንግሥት ትኩረት አናሳ መሆኑን ገልጻ በአንጻሩ የዘርፉ ባለቤቶች በራሳቸው ተነሳሽነት እየሰሩ መሆኑን የፊልም ባለሙያዋ ተናግረዋል።

በተለይ የባለሙያውን አቅም ግንባታ ለማሳደግ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ከውጪ በማስመጣት ሥልጠና መሰጠቱን ነው የተናገሩት።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ተክሉ ለፖሊሲው መተግብሪያ የሕግ ማዕቀፎችና ስትራቴጂዎች ቅድሚያ ተስጥቷቸው የሚዘጋጁ ይሆናል ብለዋል።

ከፊልም መሰረተ ልማትና ከባለሙያዎች እጥረት ጋር የሚነሱ ችግሮች ግን በሂደት የሚፈቱ መሆናቸውን አክለዋል።

የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ውስጥ የሰው ሀብት ልማት፣ የአሰራር ሥርዓት፣ የፈጠራ፣ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጉዳይ፣ ፊልም የማምረት ሥራ፣ የፊልም ሥርቆትና ገበያ ልማት ጉዳይ ተካተውበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም