ቀጥታ፡

የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ ችግር በቱሪስት ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል ተባለ

አዲስ አበባ ነሀሴ 29/2010 በኢትዮጵያ የሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮች ከውጭ አገሮች በሚመጡ ቱሪስቶች ፍሰት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩ ተጠቆመ፡፡ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ከአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ንግድ ዘርፍ ማህበራትና ኢትዮጵያ ምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች ማህበር ጋር የቱሪስት ፍሰቱን ማሳደግና የሆቴሎችን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመፍታት የሚያግዝ ምክክር በዛሬው እለት በአዲስ አበባ አካሂዷል። የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የማርኬቲንግ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ጌታቸው በምክክር መድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ ሆቴሎች በተለይም ለውጭ አገር ጎብኚዎች የሚሰጡት አገልግሎት ውስንነት አለበት። የውጭ አገር ቱሪስቶችን የሚያስተናግዱ ሆቴሎች ዘንድ የሚታየው የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ወደ አገሪቱ በሚመጡ የጎብኚዎች ቁጥር ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ የሆቴሎች ቁጥርና ደረጃ እያደገ ቢመጣም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የሚታየው ችግር በሚፈለገው ልክ እየተፈታ እንዳልሆነና አሁንም ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተለይም ጊዜው የሚጠይቀውን የመስተንግዶ አገልግሎት አገሪቱን ሊጎበኙ ለሚመጡ ቱሪስቶች በመስጠት ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የምግብ አገልግሎት ያለመስጠትና ከልማዳዊ አሰራሮች ያለመውጣት ችግሮች መኖራቸውን አቶ ሲሳይ ለአብነት አንስተዋል፡፡ ዘመኑ የሚጠይቀውን  የምግብ አዘገጃጀት ያለመገንዘብ፣ አገርኛ  ምግቦችን ፈጠራዎችን በመጠቀም ለአገልግሎት ያለማብቃትም ችግሮች እንደሚስተዋሉም ጠቁመዋል፡፡ ስለሆነም ሆቴሎች ከውጭ አገር የሚመጡ ጎብኚዎች ተገቢውንና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት የራሳቸውንም ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚኖርባቸው አቶ ጌታቸው አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም የባህል ምግቦች ላይ ፈጠራ ተጠቅመው የራሳቸውን መለያ መፍጠር ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና ለማሳደግ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ የተለያዩ አካላት ተቀናጅተው በመስራት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ሼፍ ሄኖክ ዘሪሁን በበኩላቸው በሆቴሎች የምግብ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሼፎች ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የሼፎችን አቅም በማጎልበት በሆቴሎች የምግብ መስተንግዶ ላይ የሚንጸባረቀውን ችግር መፍታት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በአገሪቱ ደረጃውን የጠበቀ የሼፎች ማሰልጠኛ ተቋም ባለመኖሩና ዘርፉ በፈጠራ ባለመታገዙ በሆቴሎች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡ ማኅበሩም ይህንን ችግር በመረዳት በአገር ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ሼፎችን ለሆቴሎች ለማብቃትና ዘርፉን ለማሳደግ ከሁለት አመት በፊት መመስረቱን ሼፍ ሄኖክ አስታውሰዋል፡፡ 400 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሼፎችን በአባልነት ያቀፈው ማህበሩ የተለያዩ ስልጠናዎችና አለም አቀፍ የልምድ ልውውጦች እያደረገ እንደሆነ ሼፍ ያሬድ ገልጸዋል። ከውጭ አገሮች የሚመጡትን ሼፎች በአገር ውስጥ ለመሸፈን ማህበሩ ደረጃውን የጠበቀ ማሰልጠኛ ተቋም ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም