ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በአግባቡ በመያዝ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በአግባቡ በመያዝ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስገነዘበ፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ካለው ከባድ ዝናብ አንጻር ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል አስፈላጊ የጥንቃቄ ስራዎች ሊከናወኑ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የረዥም ጊዜ የአየር ጠባይ አስተባባሪ አቶ በቃሉ ታመነ የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች በዋናነት የበልግ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ አካባቢዎች በዓመት ከስልሳ እስከ ሰባ በመቶ የሚሆነውን ውሃ የሚያገኙት በበልግ ወቅት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በየካቲት አጋማሽ መጀመር የነበረበት የበልግ ዝናብ ዘግይቶ መጀመሩን የተናገሩት ባለሙያው፤ ዝናቡ በአጭር ጊዜ ሊቆም ስለሚችል በአግባቡ በመያዝ ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ነው ያሉት፡፡

በተለይም ከሚጥለው ዝናብ የሚገኘውን ውሃ ለከብቶች መጠጥ ውሃ እና መኖ ለማዋል በአግባቡ መያዝ እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡ 

በአንዳንድ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ መጠን ሊጨምር ስለሚችል አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ በከተሞች አካባቢ ቅጽበታዊ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ከወዲሁ ማጽዳትና ማስተካከል እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም