መንግስት የዜጎችን በፈለጉት አካባቢ የመኖር መብት ሊያረጋገጥ ይገባል---የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የዜጎችን በፈለጉት አካባቢ የመኖር መብት ሊያረጋገጥ ይገባል---የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች
ባህር ዳር መጋቢት 15/2014 ''መንግስት የዜጎችን በመረጡት አካባቢ በሰላም ሰርቶ የመኖር መብታቸውን ሊያረጋገጥ ይገባል'' ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።
በባህርዳር ከተማ የነዋሪዎች የውይይት መድረክ ትላንት ተካሂዷል።
የባህር ዳር ከተማ የአገር ሽማግሌዎች ማህበር ሰብሳቢ ሊቀ ህሩያን በላይ መኮንን እንዳሉት፣ ለዘመናት በቆየው የኢትዮጵያ ታሪክ በህዝቦች መካከል ምንም አይነት ግጭትና ቁርሾ ኑሮ አያውቅም።
ላለፉት 27 ዓመታት በዝህቦች መካከል ትኩረት ተሰጥቶ የተሰራው የመለያየትና የጥላቻ ፖለቲካ በአሁኑ ወቅት ፍሬ አፍርቶ ለንጹሀን መገደልና መሰደድ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ህዝብ ከለውጡ በኋላም ቢሆን አገሬ ብሎ በሚኖርባቸው የተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ለከፍተኛ ሞትና ስደት እየተዳረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ህዝብ ለህዝብ መቼም ተጣልቶ እንደማያውቅ ያስታወሱት ሊቀ ህሩያን በላይ፣ "ችግሩ እየተፈጠረ ያለው ፖለቲካው ሲበላሽ በመሆኑ ልሂቃን ለህዝብ ደህንነት ተናበው መስራት ይኖርባቸዋል" ብለዋል።
መንግስት በህብረተሰቡ ውስጥ ቅሬታ እየፈጠሩ ላሉ ጉዳዮች በትኩረት አድምጦ ተገቢ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
"ዜጎች በብሔራቸውና በማንነታቸው ተመርጠው የሚገደሉበት ሁኔታ ሊቆም ይገባል'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ መሰረት ተክለሃይማኖት ናቸው።
መንግስት የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት ከማረጋገጥ ባለፈ ለህዝብ ቅሬታ ጆሮ መስጠትና አመራሩም ከሙስና የጸዳ እንዲሆን በየጊዜው ተገቢ ክተትል ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
አመራሩ ራሱን ከሙስና በማጽዳት በህዝብ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስና የመንግስትን ሀብት ለተገቢው ሥራ ግልጽነት ባለው መልኩ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ጽፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ ላይለያይ የተጋመደ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ሸኔ በክልሉ ውስጥ ብሄር ሳይለይ ግድያ በመፈጸም ህዝብን ለመፈናቀልና ለሌሎች ችግሮች እየዳረገ መሆኑን ተናግረዋል።
"በክልሉ ሸኔ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ግድያና ማፈናቀል ለመከላከል የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል" ብለዋል።
"ሸኔ ከሁሉም በላይ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ነው'' ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ "አማራን ለምን ትገድላችሁ፣ የጭካኔ ተግባሩን የሚቃወሙ በርካታ የኦሮሞ ተወላጆችን ገድሏል መግደሉን ገልጸዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በርካታ የኦሮሚያ ክልል አመራሮችን መግደሉንም አውስተዋል።
ቡድኑ የብሔር ግጭት መልክ ለማስያዝ በርካታ አማርኛ ተናጋሪ ዜጎችንና ንጹሀንን ለይቶ መግደሉንና ማፈናቀሉን አመልክተዋል።
የክልሉ አመራር ሸኔን ለማጥፋት በሚደረገው ርብረብ ዋጋ እየከፈለ መሆኑን ገልጸው፣ "ይህ ማለት ግን ከሸኔ ጋር የሚያብር አመራር ፈጽሞ የለም ብሎ መደምደም አይቻልም" ብለዋል።
በአሸባሪው ሸኔ የጥፋት ተግባር በሚሳተፉ ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ሸኔ ህወሓትን ጨምሮ ሌሎች የውጭ ሃይሎች የሚያደርጉለትን ድጋፍ በመጠቀም ክልሉን እየረበሸ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር አሸባሪ ቡድኑን የማጥፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
"ህዝቡ አምርሮ የሚያነሳቸውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና የደህንነት ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ናቸው።
ብሄር ተኮር በደልን ለመከላከል ከኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የኦሮሚያ ክልል መንግስት አሸባሪው የሸኔን ቡድን ለማጥፋት የሚቻለውን ሁሉ ከማደርግ በተጨማሪ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስ ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
"በአማራ ክልል ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር መከላከል የሚቻለው ጣት በመቀሳሰር ሳይሆን በመቀራረብና ተባብሮ በመስራት ነው" ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ከኦሮሚያና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ጋር ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፣ መንግስት ለበርካታ ዓመታት የነበሩ ችግሮችን በመፍታት የህዝቡን ሁለንተናዊ ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሸኔና የህወሀት ወራሪ ሀይል የተጀመረውን የበልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ ቢሞክሩም ኢትዮጵያዊያን ህብረታቸውን አጠናከረው ባደረጉት ትግል ዓላማቸውን ማጨናገፍ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በከተማው የተጀመሩ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅና የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።