ለኢድ አልፈጥር እና ኢድ አልአድሀ የዳያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለኢድ አልፈጥር እና ኢድ አልአድሀ የዳያስፖራ የአገር ቤት ጥሪ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው
መጋቢት 14/2014/ኢዜአ /የኢድ-አልፈጥር እና ኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን በአገር ቤት ለማክበር የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በማህበራዊ፣ ምጣኔ ሀብት፣ ፓለቲካና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ የተከናወኑ የዲፕሎማሲ ተግባራትን አስመልክተው ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ዳያስፖራው በበቃ እንዲሁም "ሆም ካሚንግ" በሚል የገና እና ጥምቀት በዓልን ወደ አገር ቤት መጥተው በተለያዩ ተግባራት ከአገራቸው ጎን መሆናቸውን እንዳሳዩ አውስተዋል።
የኢድ-አልፈጥር እና ኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን በአገር ቤት በጋራ ለማክበር ለዳያስፖራው የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በገና እና ጥምቀት ለዳያስፖራው በነበረው አቀባበልና መስተንግዶ መሰረት ለኢድ የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል አስፈላጊው ሁሉ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ለመርሃግብሩ ወደ አገራቸው የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ተቀብሎ ለማስተናገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሆኖ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በፓለቲካ ዲፕሎማሲ ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ ሰነዶች እንዳይጸድቅ ዜጎች ከሚያደርጉት የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት የአሜሪካ መንግስትን ለማስገንዘብ የማያቋርጥ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።