ቀጥታ፡

የስራ አጥነትን ችግር ለመፍታትና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ

ሆሳዕና፤መጋቢት 15/2014 (ኢዜአ) የስራ አጥነትን ችግር ለመፍታትና የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ መንግስት በትኩረት እንዲሰራ በሀድያ ዞን የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

በከተማዋ በልማትና መልካም አሰተዳደር ዙሪያ በተካሄደው ህዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ ከተሳተፉት መካከል ወጣት ሰላሙ ታደሰ በሰጠው አስተያየት፤በአካባቢው ለወጣቶች ተጠቃሚነት መረጋገጥ የሚያስፈልጉ የስራ አማራጮች እንዳልተመቻቹ ተናግሯል።

በዚህም ምክንያት ወጣቱ አማራጭ የስራ ፍለጋ በህገ ወጥ መንገድ ደቡብ አፍሪካና አረብ ሀገራት ለስደት በመዳረግ ለተለያየ ስቃይና እንግልት ከመዳረግ ባለፈ ህይወቱን የሚያጣበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቅሷል፡፡

መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ወጣቱ ያለውን እምቅ እቅምና እውቀት ተጠቅሞ በሀገሩ እንዲለወጥ የተለያየ የስራ አማራጮችን በማመቻቸት ችግሩን ለመፍታት እንዲሰራ ጠይቋል፡፡

ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ አጀቡሽ ዋካልቶ፤ ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን ለመፍጠር በዘርፉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ደረጃ ማሻሻልና ቁጥር ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢ የህዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ መጨናነቅ የሚስተዋል መሆኑን አንስተው ፤መንግስት የጤና ተቋማትን ቁጥርና ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል ፡፡

ለዘመናት መፍትሄ የታጣለት የሆሳዕና የውሃ ችግር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በአጠረ ጊዜ እንዲፈታም እንዲሁ፡፡

በከተማዋ ቀድሞ የተሰሩና ከሆሳዕና አዲስ አበባ የሚወስደው የአስፓልት መንገዶች መበላሸት በተጠቃሚው ማህበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ መምጣቱን የተናገሩት ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ግርማ ሙዘይን ናቸው፡፡

በዚህም ምክንያት በተለይ ለከፍተኛ ህክምና ወደ አዲስ አበባ የሚላኩ ህሙማንን ፈጥኖ ለማድረስ ስቃይና እንግልት እየተዳረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መንገዱ አመቺ ቢሆንም የህክምና አገልግሎት በማግኘት መዳን የሚችሉ ዜጎችን በመንገዱ ብልሽት ምክንያት ለሞት እየተዳረጉ በመሆኑ መንግስት ለመንገዱ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው ያመለከቱት፡፡

በመድረኩ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አብርሃም ማርሻሎ፤ መንግስት በህገ ወጥ ጉዞ የተለያየ ችግር እየደረሰባቸው የሚገኘውን የአካባቢውን ወጣቶች ያላቸውን የስራ ተነሳሽነት መንግስት እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡

የአካባቢውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ የልማት አማራጮች በማከናወን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ወጣቱ ያለውን እምቅ አቅም በሀገሩ ላይ እንዲያውል በልዩነት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ ከነበረው የጸጥታና መሰል ነባሪያዊ ሁኔታ ብዙ የሀገር ሀብት መባከኑ ያስታወሱት አቶ አብርሃም፤ መንግስት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የሀድያ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ ያላሰለሰ ትግል በማድረግ የሚታወቅ መሆኑን በማስታወስ የለውጡን ተግዳሮት የሆኑ አስተሳሰቦችን በመቃወም ሰላሙን አረጋግጦ እንደቆየም  አንስተዋል፡፡

ህዝቡ ለውጡ እንዲመጣ ያደረገውን ተጋድሎ ከመንግስት ጎን በመሆን ከዳር ማድረስ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም