በክልሉ የመሰረተ ልማትና የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ለትምህርት ሥራው እንቅፋት ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የመሰረተ ልማትና የሰለጠነ የሰው ሀይል እጥረት ለትምህርት ሥራው እንቅፋት ሆኗል
ሚዛን (ኢዜአ) መጋቢት 13/2014 --የመሰረተ ልማት እና ብቁ የሰው ሀይል እጥረት የትምህርት ሥራና ጥራት ላይ ችግር መፍጠሩን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ከመሠረተ ልማትና ከሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ጋር በተያያዘ ችግሮች አሉ።
ቀደም ሲል ለ27 ዓመታት ለአካባቢው ትኩረት መነፈጉ የትምህርት ሥራው በተሻለ እንዳይመራ ማድረጉን የገለጹት አቶ አልማው፣ በእዚህም የአካባቢው ማህበረሰብ ከመጎዳቱ ባለፈ አሁን ለተስተዋለው ችግር ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
ኃላፊው እንዳሉት የትምህርት መሰረተ ልማት በጥራት አለመሟላት፣ በዘርፉ የሰለጠኑ በቂ መምህራንና የትምህርት አመራር አለመኖር እንዲሁም ያለበቂ ጥናትና ዝግጅት በአካባቢው ቋንቋ የማስተማር ሥራ መጀመሩ በክልሉ የተስተዋሉ ችግሮች ናቸው።
ይህም በክልሉ የሰለጠነ የሰው ሀይል የማፍራት ሥራው ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን አቶ አልማው ገልጸዋል።
በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የዳስ መማሪያ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፣ በሌሎች አካባቢዎችም ኤሌክትሪክና ውሃ የሌላቸው ትምህርት ቤቶች መበራከት ችግሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።
ኃላፊው አንዳሉት ከመምህራን ብቃትና አቅም አንጻር በአብዛኛው የትምህርት ተቋማት ከደረጃ በታች የሆኑ መምህራን እያስተማሩ ይገኛሉ።
ለአብነት አምስተኛ ክፍልና ከእዚያ በላይ ከሚያስተምሩ 16ሺህ የሚበልጡ መምህራን ለሚያስተምሩበት የክፍል ደረጃ የሚመጥን የትምህርት ደረጃ ያላቸው 2 ነጥብ 8 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ላይ ደግሞ 28 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ቀሪ 72 በመቶ ከዲፕሎማ በታች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በተጠቀሱት ችግሮች በትምህርት ስራውና ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን አመልክተዋል
ክልሉ አዲስ የተቋቋመ በመሆኑ እስካሁን ያሉትን ችግሮች የመለየት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፣ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ማህበረሰቡን፣ ትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያቀናጀ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የመምህራንን አቅም ለማሳደግ በክልሉ ከሚገኙ የመምህራን ኮሌጆችና ዩኒርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልጠናዎች ለመስጠት ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት የሚመለከተው አካል በሙሉ በተቀናጀ መልኩ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
በክልሉ በትምህርት ሥራ ሰፊ ክፍተት ከሚታይባቸው ዞኖች አንዱ የምዕራብ ኦሞ ዞን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መላኩ ባሩማ ናቸው።
አቶ መላኩ እንዳሉት በዞኑ ካሉ 199 አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 80 ዎቹ በዳስ የተሰሩ ናቸው።
በሰለጠነ የሰው ሃይል በኩልም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው የሚያስተምሩ መምህራን የዲፕሎማ ምሩቃን ናቸው።
በአንደኛና ደረጃና በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችም የ10ኛ ክፍል ትምህርት አጠናቅቀው ወደሚቀጥለው መሻገር ያልቻሉትን አወዳድሮ በመቅጠር እንዲያስተምሩ መደረጉን ገልጸዋል።
ይህም ተማሪዎች ተገቢ ዕውቀት ጨብጠው ወደቀጣይ ክፍል እንዲያልፉ በማድረግና ተወዳዳሪነት ላይ የራሱን ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።
"በዞኑ በአራት የብሔረሰብ ቋንቋ የመማር ማስተማር ሥራ እየተካሄደ ቢሆንም ያለጥናት በመጀመሩ በቋንቋዎቹ የሰለጠኑ መምህራንን በበቂ ሁኔታ ማግኘት አልተቻለም፤ ይህም ችግሩን አግዝፎታል" ሲሉም አቶ መላኩ አክለዋል።
እንደ ሀላፊው ገለጻ በአርብቶ አደር አካባቢ በትምህርት መሰረተ ልማት አለመሟላትና ሌሎች ችግሮች ምክንያት መምህራን ተረጋግተው መስራት አልቻሉም።
በዞኑ በሁለት የብሔረሰብ ቋንቋዎች ትምህርት እየተሰጠ ቢሆንም ከመጽሐፍ ዝግጅት ጀምሮ በመምህራን በኩል ከፍተኛ እጥረት በመኖሩ መቸገራቸውን የተናገሩት ደግሞ የቤንቺ ሸኮ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ግዛው ሃይሌ ናቸው።
በቅድመ መደበኛ እና መደበኛ ትምህርት ቤቶች ካለው ብቁ የመምህራን እጥረት የተነሳ የመማር ማስተማር ስራው ለደረጃው በማይመጥኑ መምህራን እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፣ በትምህርት ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ዛሬ በትምህርት ዘርፉ እየተስተዋለ ያለው ችግር ለቤተሰብ እና ለሀገር ሸክም የሚሆን ዜጋ እንዲፈጠር ምክንያት ስለሚሆን ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት የመንግስት፣ የህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።