ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመንከባከብና የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ አበረታች ስራ እያከናወነች ነው

መጋቢት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመንከባከብና የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ አበረታች ስራ እያከናወነች መሆኑን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ገለጹ።

በአዲስ አበባ በሚገኘው የጀርመን ኢምባሲ የጀርመን መንግስት በዓለም ላይ ለሚገኙ ስደተኞች የትምህርት እድል መስጠት የጀመረበትን 30ኛ ዓመት አክብሯል፡፡

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በማስተናገድ የምትታወቅ አገር መሆኗን አንስተዋል።

ትምህርት ስደተኞችን በማብቃት ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የጀርመን መንግስት ለስደተኞች የሚሰጠውን የትምህርት እድል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ሰደተኞችን በልዩ ሁኔታ ተቀብሎ በመንከባከብና የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ የሚያስመሰግን ተግባር እያከናወነ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

ይህም ጀርመን ለስደተኞች በምትሰጠው ነጻ የትምህርት እድል ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ቀዳሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለስደተኞች የትምህርት መልካም የሆነ ፖሊሲ እንዳላት ጠቅሰው፤ በርካታ ስደተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው ጀርመን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመሆን ስደተኞች የትምህርት እድል እንዲያገኙ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሁለት አይነት የድጋፍ ፓኬጅ የተዘጋጀ ሲሆን፤ አጠቃላይ 6 ሺህ 600 ስደተኞች የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ውስጥ 4 ሺህ 500 ስደተኞች ትምህርታቸውን የተከታተሉት በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ መሆኑን ገልጸው፤ ቀሪ 2 ሺህ 100 የሚሆኑት ደግሞ በዋናነት በጀርመን መንግስትና ድጋፍ የትምህርት እድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ጀርመን በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች የትምህርት እድል መስጠት ከጀመረች ሁለት አስርተ ዓመታት መቆጠሩንም አስገንዝበዋል፡፡

በጀርመን አገር የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ማህበር ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ግዛው፤ ከጀርመን በተጨማሪ ሌሎች አገራት ኢትዮጵያ በስደተኞች ላይ እያከናወነች ያለችውን በጎ ተግባር ሊደግፉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ከጎረቤት አገራት የመጡ 900 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች እንደሚኖሩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም