ቀጥታ፡

በልማት ስራዎች ላይ የሚታዩ የጥራት ጉድለትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ነዋሪዎች ጠየቁ

ሚዛን፣ መጋቢት 14/2014 (ኢዜአ)..በልማት ስራዎች ላይ የሚታዩ የጥራት ጉድለትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈታላቸው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቤንች ሸኮ ዞን ሕዝባዊ መድረክ ተሳታፊ ነዋሪዎች ጠየቁ።

ነዋሪዎቹ ዛሬ  በሚዛን አማን ከተማ ባካሄዱት ውይይት እንዳሉት ከልማትና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ህዝቡን ለምሬትና ቅሬታ የሚዳርጉ አሰራሮች በአፋጣኝ ሊስተካከሉ ይገባል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች  መካከል አቶ ኪዳነ ነጋ እንዳሉት የህክምና ተቋማትን ጨምሮ አብዛኛቹ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር አለባቸው።

የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ጎልቶ ከሚታይባቸው ተቋማት መካከል የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቲችንግ ሆስፒታል አንዱ መሆኑን  ጠቅሰው በሆስፒታሉ ሀኪሞች የታዘዘ መድሐኒትና የህክምና መርጃ ቁሳቁስ ለማግኘት አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል።

"ህብረተሰቡ የተሟላ የህክምና አገልግሎት ማግኘት ባለመቻሉ ለእንግልትና መጉላላት እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል።

"አዲስ የተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ዋና ከተማ እስካሁን ይፋ ያልሆነበት ምክንያት ግልጽ ስላይደለ በአፋጣኝ ተወስኖ ህዝቡ አገልግሎት እንዲያገኝ ሊደረግ ይገባል" ሲሉም አቶ ኪዳነ ጠይቀዋል።

ከሚዛን -ቴፒን ጨምሮ በፌደራል መንግሥት የሚሰሩ የአስፓልት ኮንክሪት መንገዶች የመጓተትና የጥራት ችግር ያለባቸው በመሆናቸው የሚስተካከልበት መንገድ እንዲመቻች አመላክተዋል።

ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ አምሳል ነጋሽ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት በተለይ ደሀውን ማህበረሰብ እያስጨነቀ ስለሆነ መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

አካባቢው ለፍራፍሬ ልማት አመቺ በመሆኑ ምርቱን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፋላቸውም ጥያቄ አቅርበዋል።

ወጣት መንግስቱ ጋንታ በበኩሉ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እየተፈጠረ ባለመሆኑ ዘረፋና ሌብነት እየተበራከተ መመጣቱን  ጠቅሶ "መንግስት አካባቢውን ያማከለ የሥራ ዕድል ሊያመቻችልን ይገባል" ብሏል።

ለመልካም አስተዳደር ችግር መባባስ መንስኤ የሆኑ አመራሮች ተለይተው የእርምት እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ የተባሉ ተሳታፊ ናቸው።

ሌሎችም የመጠጥ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር እንዲፈታም ከመድረኩ ተሳታፊዎች ጥያቄ ቀርቧል።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ  ከመድረኩ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በዘረፋና በሌብነት ተሰማርተው ህዝቡን እያሰቃዩ ያሉ ቡድኖችና ግለሰቦች ላይ ክትትል በማድረግ  እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

"የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ቲቺንግ ሆስፒታልን ጨምሮ በሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚታየውን የአሠራር ግድፈቶች በማረም መፍትሄ ለማበጀት አጥብቀን እንሰራለን" ብለዋል።

ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት የሆኑ የትራንስፖርት፣ ነዳጅ ማደያዎችና የንግድ  ተቋማት የሚታየውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴና ድርጊት ለማስቆም በየደረጃው ጠንካራ ቁጥጥርና እርምጃ የመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ምክትል አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ ላነሳው የክልል መቀመጫ ዋና ከተማ ጉዳይ በተመለከተም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው  በሰጡት ምላሽ ክልሉ አራት ማዕከላት ማለትም በቦንጋ፣ ሚዛን፣ ቴፒና ተርጫ ከተሞች ይኖሩታል።

አሁን ላይ ማዕከላቱን በማዋቀር ለህዝቡ ተደራሽ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ክላስተር ለመፍጠር  ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ጥናቱ እንዳለቀ በህዝብ ተገምግሞ ወደ ተግባር እንደሚገባ ነው አቶ ማስረሻ ያረጋገጡት።

የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ  ከከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር በክልሉ ለግብርና ልማት አመቺ የሆነውን ሰፊ መሬት  ወጣቶችን በማደራጀት ልማት ውሰጥ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ለተነሱት ቅሬታዎችም በተመለከተ በክልሉ  የኤሌክትሪክ ኃይል ሪጂን ለማቋቋም  በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው "ሪጅኑ ሲቋቋም ችግሩን በቅርበት በመከታተል በጋራ የምንፈታው ይሆናል" ብለዋል።

ከመንገድ ግንባታ መጓተትና ጥራት ጋር በተያያዘም ከሚመለከታቸው የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ጋር በቀጣይ ንግግር እንደሚደረግበት አብራርተዋል።

መድረኩን የመሩት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው ዞኑ ካለው እምቅ የተፈጥሮ ሀብትና ጸጋ አንፃር  የሀገሪቱን ልማት ለማጠናከር ትልቅ አቅም እንደሚሆን ገልጸው  አቅሙን ለማዳከም የሚሰሩን የጥፋት ኃይሎች ህዝቡ ሊታገላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ዓለም አቀፍ ክስተት ነው" ያሉት ዶክተር ቢቂላ "ህገ ወጥና ስግብግብ ነጋዴዎች ሚና እንዳባባሰው  ግን አይካድም" ብለዋል።

እንደ ሀገር የፍጆታ ምርቶች ሥርጭት ህግና ሥርዓትን እንዲከተል ለማድረግ ጥረት መጀመሩን ገልጸው ጥረቱን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ደላሎችን ተቆጣጥሮ ፈር ማስያዝ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተጓዷኝም በዋናነት የጓሮ አትክልቶችን በግለሰብ ደረጃ በማምረት የቤተሰብ ፍጆታን በመሸፈን ገበያን በዘላቂነት ለማረጋጋት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተቀመጠው አቅጣጫ ተፈጻሚነት ሁሉም እንዲተጋ አሳስበዋል።

የአካባቢውን የምርት አቅም የሚመጥን የፍራፍሬ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ እንዲተከል ጥራት ያለው ከፍተኛ ምርት ለማምረት አርሶ አደሩ ጠንክሮ ከሰራ ዕድሉ በመንግሥት እንደሚመቻች አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ህብረተሰቡ ያነሳቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች የመንግስት እቅድ አካል በማድረግ በሂደት ለመፍታት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም