የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቆየበት የሰላም እጦት ወጥቶ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት እንዲመራ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቆየበት የሰላም እጦት ወጥቶ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት እንዲመራ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል
መጋቢት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቆየበት የሰላም እጦት ወጥቶ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት እንዲመራ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ ከተማ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ወኪሎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በመሩት የውይይት መድረክ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ባለሃብቶችና የተለያዩ የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቆየበት የሰላም እጦት ወጥቶ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት እንዲመራ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
በተለያዩ አካላት በተሸረቡ ሴራዎች ባለፉት ዓመታት የከፋ የሰላም አጦት ጋጥሟል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።
በአዲስ አበባም ቢሆን ሕዝቡ ማልዶ መውጣትና አምሽቶ መግባት በማይችልበት ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላማዊ ህይወት እንዲመራ ከገዢው ፓርቲ ጀምሮ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮችና የማሕበረሰብ አንቂዎች በሕዝቡ አብሮነት ላይ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የተነሱት ችግሮች በአንድ ጊዜ ባይፈቱም በሂደት እልባት የሚያገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።
አንዳንዱ ችግር መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስፈልገው በመሆኑ ጊዜ የሚወስድና የአስተሳሰብ ለውጥ ጭምር የሚፈልግ መሆኑንም አስረድተዋል።
ቅንነትና የጋራ ርብርብ ካለ በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው በጊዜ ሂደት የማይፈታ ችግር እንደሌለ ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው በሕዝብ ወኪሎቹ የተነሱ ጉዳዮች በእቅድ ተይዘው ተፈጻሚ ይሆናሉ ብለዋል።
ከሰላም እጦት፣ ከሌብነት፣ ከብልሹ አሰራር፣ ከስራ አጥነትና ከኑሮ ውድነት ጋር የተነሱ ችግሮች በአግባቡ ተይዘው ይፈታሉ ብለዋል።
በተጨማሪም 'ውስጣችሁን ፍትሹ፣ አመራራችሁን አጥሩ፣ ከሪፖርት በዘለላ ወደ ታች ወርዳችሁ አረጋግጡ' ያላችሁት ተገቢ ግብአት ነው እንወስደዋለን ብለዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ