በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንደኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት ተበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንደኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት ተበረከተ
መጋቢት 14/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና አንደኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት አበረከተ፡፡
ኢትዮጵያ ከመጋቢት 9 እስከ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በሰርቢያ ቤልግሪድ በተደረገው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር በአራት ወርቅ፣ ሶስት ብር እና ሁለት የነሀስ ሜዳሊያዎች ከዓለም አንደኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ውጤቱም የኢትዮጵያ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር የምንጊዜም ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
በውድድሩ ለተሳተፉ የልዑካን ቡድን አባላት በዛሬው እለት ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም የማበረታቻ ገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡
በዚህም ፌዴሬሽኑ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ለሆኑ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 40 ሺህ ብር፣ የብር ሜዳሊያ ላመጡ 25 ሺህ ብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ ለሆኑት ደግሞ 15 ሺህ ብር ሽልማት አበርክቷል።
በተጨማሪ ዲፕሎማ ይዘው ላጠናቀቁ አትሌቶች 10 ሺህ ብርና በተሳተፎ ብቻ ለተመለሱ ደግሞ 5ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል።
ለአትሌት አሰልጣኞችም እንደየውጤታቸው የገንዘብ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን፤ ለሌሎች የልዑክ ቡድኑ አባላትም ሽልማት ተሰጥቷል።
በውድድሩ በ3 ሺህ ሜትር ተካፍሎ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሰዓት ያላቸው አትሌቶች መመረጣቸውና አትሌቶቹ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸው ለውጤቱ መመዝገብ ከፍተኛ ሚና እንዳበረከተ ተናግሯል፡፡
በውድድሩ ለተካፈሉ አትሌቶች የተደረገው አቀባበል እጅግ አስደሳች ነበር ብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም ለቤት ውስጥ ውድድሮች ብዙም ትኩረት እንደማይሰጥ አስታውሶ፤ በዘንድሮው ዓመት ግን እንደ ኦሊምፒክና ዓለም ሻምፒዮና ሁሉ በውድድሩ ለተሳተፉ አትሌቶች ደማቅ አቀባበል መደረጉን ገልጿል፡፡
የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አክሱማዊት አምባዬ ያልጠበቁት ደማቅ አቀባበል እንደጠበቃቸው ገልጻ፤ የተደረጉ ማበረታቻዎች በቀጣይ ለሚደረጉ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የበለጠ ተነሳሽነት እንደሚፈጥሩ ተናግራለች፡፡
በ1 ሺህ 500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ያመጣው አትሌት ሳሙኤል ተፈራ በበኩሉ ከዚህ ቀደም በቤት ውስጥ ውድድር አሸናፊ እንደነበር አስታውሶ፤ በወቅቱ ለውድድሩ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ እንደነበር ነው የገለጸው።
በዘንድሮው ዓመት ግን ለቀጣይ ውድድሮች ተነሳሽነትን በሚፈጥር መልኩ ማበረታቻዎች መደረጋቸውን ገልጿል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በውድድሩ ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች መላ ኢትዮጵያዊንን የሚያኮራ ውጤት ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል።
"በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን የመንፈስ ጥንካሬና ጠንክሮ ልምምድ መስራትን ይጠይቃል፤ እናንተም ይህንን በተግባር አሳይታችኋል" ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አትሌቲክስን ጨምሮ ሌሎችን የስፖርት ዘርፎች ለመደገፍ እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በውድድሩ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት ሽልማት 770 ሺህ ብር ወጪ ማድረጉም በመርሃ-ግብሩ ተገልጿል፡፡