የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ከምርት እና አገልግሎት ሽያጭ ከ271 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ከምርት እና አገልግሎት ሽያጭ ከ271 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ
መጋቢት14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከምርት እና አገልግሎት ሽያጭ 271 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።
የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል፤ የተቋሙን የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አብዛኛዎቹ የልማት ድርጅቶች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ እና ወቅታዊ ሀገራዊ የፀጥታ ችግሮችን በመቋቋም ትርፋማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከምርት እና አገልግሎት ሽያጭ 271 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።
ከታክስ በፊት 51 ነጥብ 9 ቢሊዮን ትርፍ መገኘቱን ጠቅሰው ካለፈው በጀት ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ እንዲሁም የኮሙኒኬሽንና ፋይናንስ ዘርፎች በግማሽ ዓመቱ ትርፋማ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ ፐልፕና ወረቀት አክሲዮን ማህበር ኪሣራ ስለማስመዝገባቸውም ጠቅሰዋል።ድርጅቶቹ ትርፋማ ያልሆኑት በውጭ ምንዛሬና የጥሬ እቃ እጥረት አጋጥሟቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የኃይል መቆራረጥ በምርትና አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ ከማስከተሉም በላይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያጋጠመው የፀጥታ ችግር ለልማት ድርጅቶቹ ሌላኛው ፈታኝ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የልማት ድርጅቶች ለሀገራዊ ጠቅላላ ምርት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እያደገ መምጣቱንና ገበያውን የማረጋጋት ሚናቸውን እየተወጡ ነው ብለዋል።
ተቋሙ በግማሽ ዓመቱ ለስኳር ኮርፖሬሽንና ኬሚካል ኮርፖሬሽን የ54 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ሀገር ብድር ክፍያ በመፈጸም ዕቅዱን ማሳካቱን ገልጸዋል።
ሆኖም 357 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ብድር ለመክፈል አቅዶ 96 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር መክፈሉን ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ ብድር ክፍያ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ የሆነው የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በዕቅዱ መሠረት ክፍያ ባለመፈጸሙ መሆኑንም አመልክተዋል።
የመንግሥት ትርፍ ድርሻ ክፍያ የሚጠበቅባቸው ድርጅቶችን በመለየትና አፈጻጸሙን በመከታተል 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉንም ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የልማት ድርጅቶቹ በግማሽ ዓመቱ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የ2 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል ብለዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶች የዞታና አስተዳደር በስሩ 36 የልማት ድርጅቶችን ያቀፈ ሲሆን በእነዚሁ ተቋማት አማካይነት በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ከ12 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል።
የልማት ድርጅቶቹ በትራስፖርትና ሎጀስቲክስ፣ በኮሙኒኬሽን፣ በፋይናንስ አገልግሎት፣ በማማምረቻ ኢንዱስትሪና በማዕድን፣ በእርሻና የግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በግንባታ እንዲሁም በንግድና አገልግሎት ዘርፍ መሰማራታቸውን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።