ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 ሰላምና ዲሞክራሲን ከማስፈን ይልቅ የኢትዮጵያውያንን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 ሰላምና ዲሞክራሲን ከማስፈን ይልቅ የኢትዮጵያውያንን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው
መጋቢት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ህጎች በሀገሪቱ ሰላምና ዲሞክራሲን ከማስፈን ይልቅ የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ መሆናቸውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አሜሪካ ይህንን በመገንዘብ ረቂቅ ህጎቹን ውድቅ እንደምታደርጋቸው እምነታቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በውይይቱ ወቅት ለትግራይ ክልል የሚደረገውን የሰብአዊ ድጋፍ አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
በክልሉ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታን አቅርቦት እንዲኖር መንግስት ቁርጠኝነት ያለው ቢሆንም ህወሓት በአጎራባች ክልሎች ላይ እያደረሰ ባለው ትንኮሳ ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ ፍሰቱ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ስላለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በተመለከተ ያነሱት አቶ ደመቀ፤ ኤችአር 6600 እና ኤስ 3199 የተሰኙ ረቂቅ ህጎች የሁለቱን የሀገራቱን የቆየ እና ታሪካዊ ግንኙነት የማያንፀባርቁ ናቸው ብለዋል።
ረቂቅ ህግጋቱ በሀገሪቱ ሰላምና ዲሞክራሲን ከማስፈን ይልቅ የኢትዮጵያውያንን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን በመገንዘብ በአሜሪካ በኩል ውድቅ ሊደረጉ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የወሰዳቸውን አበረታች የሰላም እርምጃዎችን አስመልክተውም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያይዘም ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎች ከእስር መፈታት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜው ሳይደርስ አስቀድሞ መነሳቱን፣ ብሔራዊ የውይይት ኮሚሽን በማቋቋምና ኮሚሽነሮችን በመምረጥ ረገድ እስካሁን የተወሰዱ አወንታዊ እርምጃዎችን ጠቅሰዋል።
ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የወሰዳቸውን አወንታዊ እርምጃዎችን በተመለከተ ሀገራቸው በአድናቆት የምትመለከተው እና እውቅናም የምትሰጠው መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል። ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ