በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ማስታወቂያዎች ተገቢነታቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ማስታወቂያዎች ተገቢነታቸውን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥምምነት ተደረገ
መጋቢት 14/2014/ኢዜአ/ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ የምግብና ሌሎች የምርት አይነቶች ተገቢነታቸውን ለማረጋገጥና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥምምነት ተደረገ።
ሥምምነቱን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስና የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሔራን ገርባ ፈርመውታል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እንድሪስ እንደገለጹት፤ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም በበይነ መረብ የሚተላለፉ የሚያሳስቱ ማስታወቂያዎች ተበራክተዋል።
ይህም በኅብረተሰቡ ጤና፣ በዕለት ተዕለት አኗኗር ላይ እንዲሁም በአገሪቱ በሚከናወነው ፍትኃዊ የንግድ ውድድር ላይ የራሳቸውን ተጽእኖ እያሳደሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህንንም ለመከላከል ባለሥልጣኑ በመገናኛ ብዙኃን የሚሰራጩ ማስታወቂያዎች በተለያዩ ዘርፎች አሉታዊ ተጽእኖ የማያሳድር መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ባለሥልጣኑ በምግብ፣ መድሃኒትና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ምርቶች በመገናኛ ብዙሃን ሲተዋወቁ ተገቢውን ጥራት የጠበቁ ሆነው እንዲተላለፉ ለማስቻል ከኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን ጋር ሥምምነት ማድረጉን ተናግረዋል።
ሥምምነቱም በባለሥልጣኑ ጥራትና ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሁም ደረጃ የወጣላቸው ምርቶች ያለ ግነት እንዲተዋወቁ በልካቸውና ኅብረተሰቡ ያልሆነ መረጃ እንዳያገኝ ያስችላል ብለዋል።
የምግብና መድሃኒት ጉዳዮችን በማስመልከት የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች በምን አይነት አግባብ መተላለፍ እንዳለበት አቅጣጫ ያስቀምጣልም ነው ያሉት።
ሥምምነቱ ሕግ በሚተላለፉ አካላት ላይም አስፈላጊውን ቁጥጥር ለማድረግና ተጠያቂነትን ለማስፈን ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው ሥምምነቱ ባሥልጣኑ በተለያዩ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ መሆናቸውን አለመሆናቸውን የሚያደርገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራን ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።
በቀጣይም የተደረገውን ሥምምነት ወደ መሬት በማውረድ በምግብ፤ መድሃኒት እና ሌሎች ተያያዥ ምርቶች ላይ በሚሰሩ ማስታወቂያዎች ተገቢነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።