ቀጥታ፡

በመጪው ወር በአንዳንድ ቦታዎች ነጎድጋድና በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ይጠበቃል-ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ

አዲስ አበባ ነሃሴ 29/2010 በመጪው መስከረም በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች ነጎድጋድና በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ  ኤጀንሲ አስታወቀ። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ግን መጠኑ መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ መጣሉን ይቀጥላል። ዝናቡ በአብዛኛው ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሄራዊ ክልሎች ውስጥ በጊዜው ለሚከናወኑ የግብርና እንቅስቃሴዎች ገንቢ ሚና ይኖረዋል ሲል ኤጀንሲው ዛሬ ለኢዜአ ገልጿል። ሆኖም ከባድ ዝናብ በሚጠበቅባቸው አካባቢዎች እርጥበቱ ከመጠን በላይ ሊሆን ስለሚችል የአርሻ ማሳዎች ላይ ውሃ እንዳይተኛ የመከላከልና ማሳውንም በወቅቱ የማረም ተግባር ማከናወን እንደሚገባም ኤጀንሲው መክሯል። የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በረባዳማ፣ ውሃ ገብና በወንዝ ዳርቻዎች ባሉ ማሳዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስሊሚችልም የመከላከል እርምጃዎች አስቀድመው እንዲወሰዱም አስጠንቅቋል። በአብዛኛው የሰሜንና የሰሜን ምዕራብ የአገሪቱ ተፋሰሶች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ የትንበያ መረጃው ጠቁሟል። መሬቱ ውሃ የጠገበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የወንዞች ሙላትና ከፍተኛ ጎርፍ በዝቅተኛ ቦታዎች ሊከሰት ስለሚችል ማህበረሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስቧል። ከመጪው መስከረም ወር አጋማሽ በኋላ ደግሞ ለረጅም ጊዜ ደረቅ ሆነው የሰነበቱ ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ ዝናቡ እንደሚጠናከር የሚጠበቅ ሲሆን የደቡብ ኦሮሚያና የደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ቦታዎች ዝናብ ማግኘት ይጀምራሉ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም