በቻይና በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
መጋቢት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በቻይና በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶኛል፤ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ከልብ የመነጨ መጽናናትን እመኛለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በላኩት የሐዘን መግለጫ አስታወቁ።
በበረራ ቁጥር MU735 ከኩሚንግ ከተማ ወደ ጉዋንዡ እየተጓዘ የነበረውና የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ ንብረት የሆነው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ከትናንት በስቲያ መከስከሱ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ የተማሰቸውን ጥልቅ ሀዘን በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እንዲሁም በራሳቸው ስም ለቻይና ሕዝብና መንግስት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በላኩት ደብዳቤ በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀዘን መግለጫቸው ለፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ መልካም ጤንነትን እና ‘ለሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና’ ሰላም፣ እድገት እና ብልጽግናን ተመኝተዋል።
የቻይና መንግስት በአውሮፕላን አደጋው ሕይወታቸው ያጡና የተጎዱ ሰዎች ቁጥርና የአደጋውን መንስኤ በተመለከተ እስካሁን በይፋ የገለጸው ነገር ባይኖርም የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ አደጋውን ተከትሎ ያሉትን ሁሉንም ቦይንግ 737-800 አውሮፕላኖች እንዳይበሩ ማገዱ ይታወሳል።