የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል የአየር ሁኔታ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያዎችን ተከታትሎ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል የአየር ሁኔታ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያዎችን ተከታትሎ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል
መጋቢት 14/2014/ኢዜአ/ የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል የአየር ሁኔታና ፀባይ ለውጥ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያዎችን ተከታትሎ ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አሳሰበ።
የሜትሮሎጂ ቀን በዓለም ለ71ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በአየር ሁኔታና ጠባይ ለውጥ ላይ የሚሰጡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያዎች ጠቃሚ ናቸው።
ይሁንና እነዚህን የማስጠንቀቂያ ትንበያዎች ተከታትሎ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸው ይህም የተለያዩ ችግሮች እያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን ክፍተት ለመሙላትና ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ከወዲሁ ለመቀነስ ከዘርፉ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አገሪቱ የያዘችውን ሁሉን አቀፍ እድገት ለማስቀጠል በሜትሮሎጂ ባለሙያዎች የሚሰጡ ዘመናዊ ትንበያዎችን ተከታትሎ ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህንንም በማድረግ በአገሪቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የድርቅና የጎርፍ አደጋዎችን መከላከል ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ክንፈ ሃይለማሪያም በበኩላቸው ለበርካታ ጊዚያት የሚሰጡ የቅድመ ትንበያ ጥቅም ላይ አይውሉም ይላሉ።
በተለይም በዘርፉ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር መዳከም ማስጠንቀቂያዎቹ ተግባራዊ እንዳይሆኑ ምክንያት መሆኑን ገልጸው ይህም በርካታ አደጋዎች እንዲከሰቱ አድርጓል ብለዋል።
ይህም ችግር መቀረፍ እንዳለበት ጠቁመው ተቋሙም በቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያዎች በኩል የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም ከአተገባበር ጋር የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ለማስቀረትም የብሔራዊ አየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በማዕቀፉ በተለይ የግብርናና ጤና የአደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር የአካባቢ ጥበቃና ሌሎች 10 የሚደርሱ ሴክተሮች ጋር ችግሩን ለማስወገድ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋት ተፈራርመው ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።