ቀጥታ፡

የባንክና ፋይናንስ ተቋማት አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል አዲስ ስትራቴጂ ቀርጸው ሊሰሩ ይገባል

መጋቢት 14/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ የባንክና ፋይናንስ ተቋማት አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው ለመቀጠል አዲስ ስትራቴጂ ቀርጸው ሊሰሩ እንደሚገባ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ።

ኢትዮጵያ ለአለም አቀፍ ባንኮች ለአመታት ዝግ አድርጋ የነበረውን ዘርፍ ክፍት የምታደርግበት ጊዜ የራቀ እንደማይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸው ይታወሳል።

የባንክ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ሲደረግ ግን የኢትዮጵያ ባንኮች በውድድር ለመዝለቅ የተደራጀና የተቀናጀ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በርካታ የዘርፉ ምሁራን የሚመክሩትም ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሆነው ለመዝለቅ ዘመናዊ አሰራር፣ የሰለጠነ የሰው ሃይል እና የተቋማትን የጋራ ጥረት ይጠይቃል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ስራ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ዳኪቶ አለሙ፤ ግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) እየተስፋፋ በመጣበት ዘመን በር ዘግቶ በመቀመጥ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይቻል ያስረዳሉ።

በመሆኑም ኢትዮጵያ የባንክ ሴክተሩን ለውጭ ባንኮች ክፍት ለማድረግ ማሰቧ ተገቢነት ያለው መሆኑን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ባንኮች በአለም አቀፍ ደረጃ የአንድን ባንክ ጠንካራነት በሚለካበት የካፒታል መጠን ከ75 በመቶ በላይ የካፒታል መጠን ችግር እንዳሌለባቸው ባደረጉት ጥናት ማረጋገጣቸውንም ዶክተር ዳኪቶ ገልጸዋል።

በካፒታል መጠን ችግር አይኑርባቸው እንጂ ከአስተዳደርና ተወዳዳሪነት አኳያ ግን ውስንነት እንዳለባቸው አብራርተዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን አዲስ ስትራቴጂ በመንደፍ፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን የማቅረብና አስተዳደርን የማዘመን ስራ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በደቡብ አፍሪካ ስዌኔ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሃላፊና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ፤ በአገር ውስጥ ባንኮች ብቻ ግዙፍ ምጣኔ ሃብት መገንባት እንደማይቻል ያስረዳሉ።

ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ለውጭ ባንኮች በራቸውን ክፍት ያደረጉ የአፍሪካ አገሮች በኢንቨስትመንት ፍሰትና ሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ የሆኑባቸውን ማሳያዎች በመጥቀስ ኢትዮጵያም ይህንኑ መከተል አለባት ብለዋል።

የኢትዮጵያም ባንኮች በዘመናዊ አሰራር ራሳቸውን በማደራጀት ተወዳዳሪ ከሆኑ የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ ሲሉም አስረድተዋል።

የውጭ አገር ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከካፒታል ማርኬት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝትና ሌሎችም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የውጭ ባንኮች ይዘውት የሚመጡትን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የአገር ውስጥ ባንኮችም ማግኘት ከቻሉ ተወዳዳሪ ከመሆን ባለፈ የተሻለ እድገት የማስመዝገብ እድላቸው ሰፊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣይ ለምትገነባው ግዙፍ ምጣኔ ሃብት የባንክ ዘርፉን መጠናከር ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል ግን የዝግጅት ጊዜ መስጠት፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መምከር፣ የውጪዎቹ የሚገቡበት መንገድ በፖሊሲና መመሪያ በደንብ መታየት አለበት ሲሉ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም