በአንድ ዓመት ውስጥ ለ211 ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ዓመት ውስጥ ለ211 ሰዎች የተሳካ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ተደርጓል

መጋቢት 14/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ለ211 ሰዎች የተሳካ የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ መደረጉን የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ገለጸ።
የዓይን ንቀለ ተከላ እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ጠቁመው ኅብረተሰቡ የዓይን ብሌን እንዲለግስ ተቋሙ ጥሪ አቅርቧል።
በኢትዮጵያ አይን ባንክ የግንዛቤ አስተባባሪ አቶ ነጋ ደምሴ እንደገለጹት፣ የባንኩ ዋና አላማ ሊድን በሚችል የአይን ብሌን ጠባሳ የሚመጣ ማየት አለመቻልን መከላከል ነው።
በኢትዮጵያ ያለውን በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት የሚከሰተውን ዓይነ-ስውርነት ለማጥፋት በርካታ የአይን ብሌን የማሰባሰብ ሥራዎችን ባንኩ እያካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንንም ተከትሎ ተቋሙም ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን የዓይን ብሌን በመሰብሰብ ንቅለ ተከላውን ለሚያከናውኑ የሕክምና ተቋማት እያሰራጨ መሆኑን ነው የገለጹት።
ለአብነትም ባለፈው የፈረንጆች ዓመትም እነዚህ ተቋማት ለ211 ሰዎች የተሳካ የአይን ብሌን ንቅለ ተከላ በማድረግ ብርሃናቸውን እንዲያገኙ መደረጉን ነው የጠቆሙት።
የዓይን ብሌን ጠባሳ የሰው ልጆችን ሙሉ ለሙሉ ማየት የተሳናቸው ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸው ነገር ግን ሕክምና ካገኘ ሊድን የሚችል ተናግረዋል።
የዓይን ጠባሳ ሊድን የሚችለው ሰዎች ከህልፈታቸው በኋላ በሚለግሱት የዓይን ብሌን መሆኑን ተናግረው ኅብረተሰቡ ዓይን ብሌኑን እንዲለግስ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንንም ተከትሎ ስለ ዓይን ብሌን ልገሳ በማስተማር ከህልፈት በኋላ የአይን ብሌናቸውን እንዲለግሱ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እያደጉ ቢመጡም የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።
ይህንንም ችግር በቀጣይ ለመፍታትና ተቋሙም በአደረጃጀት የሚስፋፋበት ጉዳይ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስረድተዋል።
ተቋሙ ባለፉት 18 ዓመታት ለ2 ሺህ 730 ኢትዮጵያውያን የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ አካሂዷል።