ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010  በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሩጫ ውድድር ላይ ህብረተሰቡ ሰፊ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ። የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት እንዳስታወቀው ሩጫው ግንቦት 19 ቀን 2010 ይካሄዳል። በጽህፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም  ሩጫውን አስመልክቶ እንዳሉት ሩጫው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለግድቡ ያለውን ድጋፍና አንድነቱን የሚያሳይበት ነው። ከዚህ በፊት ሩጫውን ለማካሄድ ሚያዝያ 21 ቀን 2010 ዓም ታቅዶ እንደነበርና በመስሪያ ቤቶች ያለውን የቲሸርት ፍላጎት ለማወቅ የተደረገው እንቅስቃሴ ከተጠበቀው በላይ ጊዜ በመውሰዱና የህትመት ችግር በማጋጠሙ መራዘሙን አመልክተዋል። በመሆኑም የፊታችን ግንቦት 19 ቀን 2010  በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ሰዓት ሩጫውን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም  አስታውቀዋል። ለሩጫው ተሳታፊዎች 250 ሺህ ቲሸርት እየተዘጋጀ ሲሆን ከወዲሁ ጥያቄ ላቀረቡ መስሪያ ቤቶች 30 ሺህ ቲሸርት መሰራጨቱን አስታውቀዋል። በሩጫው መሳተፍ ለሚፈልጉ ሌሎች አካላት ደግሞ ቲሸርት የሚሸጥባቸው ማእከላት በቅርቡ ይፋ የሚደረግ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በፖስታ ቤቶች በኩል ስርጭት መጀመሩንም አመልክተዋል። "እኔም አሻራዬን አኑሬያለሁ" የሚል መልዕክት የሰፈረበት 250 ሺህ የደረት ፒን ተዘጋጅቷል፤ ከዚህ ውስጥም 30 ሺህ ያህሉ ተሰራጭቷል። ህብረተሰቡ ቲሸርቱን በ100 ብር ፣ የደረት ላይ ፒኑን ደግሞ በ50 ብር በመግዛት ተሳታፊ እንዲሆን ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም