ቀጥታ፡

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በመደገፍ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የሚጠበቅብንን ሚና እንወጣለን-የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች

መጋቢት 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በመደገፍ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የሚጠበቅብንን ሚና እንወጣለን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ፡፡

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩም ነው ድርጅቶቹ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ለኢትዮጵያ ህዝብ ፕሬዝዳንት ጋሻው ሽባባው ጥምረቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ 364 ድርጅቶችን በአንድነት የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥምረቱም በዋናነት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት የተዋቀረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የተሻለ አበርክቶ እንዲኖረው ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ጥምረቱ ለምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ የሚሆን ግብዓት በማሰባሰብ ረገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት ሲሰራ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በኮምሽነሮች ምርጫ ወቅትም አስፈላጊውን ጥቆማ በማድረግ የሚጠበቅበትን ተሳትፎ ማድረጉንም እንዲሁ።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአገራዊ ምክክሩ ላይ የሚኖራቸውን ኃላፊነት በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ አሰራሮችን የመዘርጋት ስራ ተጀምሯል ነው ያሉት።

ጥምረቱ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ካደረገው ተሳትፎ መልካም ተሞክሮ በመውሰድ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በተሻለ መልኩ ለመስራት በቂ ዝግጅት ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣የማህበረሰብ አንቂዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በምክክሩ ላይ ተሳትፏቸውን ለማጎልበት ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለባቸውም ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮች ከዘመናት በፊት ሲንከባለሉ የመጡና መፍትሔ ሳይሰጣቸው የቆዩ ናቸው ይላሉ፡፡

ችግሮቹን በምክክር መፍታት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ መወሰኑ ተገቢና ትክክለኛ የመፍትሄ አቅጣጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮች ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሊተጉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያዊነት የዜጎች ማስከበሪያ ጉባኤ ሰብሳቢ ዶክተር እርቁ ይመር ለዘመናት ሳይፈቱ የመጡ ችግሮች የግጭት መንስኤ መሆን ከጀመሩ ሰነባብተዋል ነው ያሉት።

በዚህም በተለይ በአብሮነትና አንድነት ላይ የተመሰረቱ አገር በቀል እውቀቶችን ለትውልዱ ማስተላለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ድርጅቱ በዋናነት በዜጎች የሚነሱ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የማመቻቸት ዓላማ ይዞ መቋቋሙን ጠቅሰው፤ ከዚህ አንጻር ለምክክር ኮምሽኑ ድጋፍ በማድረግ ለተቋቋሙለት ዓላማ ስኬት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጰያ ከ3 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው በስራ ላይ እንዳሉ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም