ቀጥታ፡

ዜጎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ ተጠየቁ

ደሴ መጋቢት 14/2014 (ኢዜአ) ዜጎች ኢትዮጵያ ወደ ሃገር ውስጥ የምታስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጠየቁ።

ኢተርፕራይዙ ከባለድርሻ አካላት ጋር በደሴ ከተማ ወይይት እያካሄደ ነው፡፡

የኢንተርፕራይዙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ በርጋ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገሮች የሚተርፍ ሀብትና ጥሬ እቃ ያላት ሀገር ናት።

"ነገር ግን ሀብቱን በአግባቡ ባለማልማቷ አገሪቱ በዓመት በአማካይ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እያገኘች ቢሆንም፤ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የውጭ ምርቶች በማስገባቷ  ኢኮኖሚው እየተጎዳ ነው" ብለዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች የወጪና ገቢ ምርቶች እንዲጣጣሙና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ኢንተርፕራዞች በአነስተኛ ድጋፍ ሊያመርቷቸው የሚችሉ ምርቶች ሁሉ ከውጭ እየመጡ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጳውሎስ፣ ለዚህም ዜጎች በሚችሉት አቅም ኢንተርፕራይዞችን እንዲደግፉና እንዲያበረታቱ ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶች እንዲጠቀም ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑንና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት "ኢትዮጵያ ታምርት" የሚል አዲስ ንቅናቄ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የመከላከያ ስራዊት ዩኒፎርምን ጨምሮ የፖሊስ፣ የተማሪዎች የሌሎች የደንብ ልብስና ጫማ በሀገር ውስጥ ኢንተርፕራዞች እየተመረቱ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡

"በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከውጭ ሊመጣ የነበሩትን 800 ሺህ ጫማ በሀገር ውስጥ በኢንተርፕራይዞች  በማስመረቱ 'የሚደነቅ፣ ጥሩ ጅምር፣መልካም ተሞክሮ'' በመሆኑ ማስፋት ይገባል" ብለዋል።

በአማራ ክልል ብቻ በሽብር ቡድኑ ለተዘረፉና ለወደሙ 108 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ልዩ ድጋፍና እገዛ እየተደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ በበኩላቸው በክልሉ ያሉ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍና በመከታተል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ያለውን ምቹ የተፈጥሮ ሀብትና ጥሬ ዕቃዎች ለመጠቀም አቅም ያላቸውን ባለሃብቶች በመሳብ በሲሚንቶ፣ በማዕድን ልማትና በሌሎችም መስኮች መሰማራታቸውን አስረድተዋል።

''ኢንተርፕራይዞችን ለማበረታታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥረት እያደረግን ነው'' ያሉት ደግሞ የዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሹመት ጥላሁን ናቸው።

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ውይይት ከአማራ ክልል ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ አመራሮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከ48 ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች  ከ600 ሺህ በላይ የሥራ እድል መፍጠራቸውን ከኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም