የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ከግቡ እንዲደርስ ሁሉም በአንድነት መንፈስ ሊረባረብ ይገባል - አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ - ኢዜአ አማርኛ
የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ከግቡ እንዲደርስ ሁሉም በአንድነት መንፈስ ሊረባረብ ይገባል - አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ
ጎንደር ነሐሴ 29/2010 ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ክብሯና ነጻነቷ እንድትመለስ የተጀመረው አዲስ የለውጥ ጎዳና ከግቡ እንዲደርስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መንፈስ ሊረባረብ እንደሚገባ አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ አሳሰበች፡፡ ለአርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆና የሙያ አጋሮቿ ትናንት ምሽት ጎንደር ከተማ ሲገባ በህዝቡ ደማቅ አቀበበል ተደርጎለታል፡፡ በከተማው ላድማርክ ሆቴል በተዘጋጀው የአቀባበል ስነ-ስርአት ላይ አርቲስት አለምጸሃይ ወዳጆ እንደተናገረችው ለውጡ ገና ያልተረጋጋና ብዙ መንገድ መጓዝ ያለበት በመሆኑ ህዝቡ ለለውጡ ቀጣይነት መረባረብ ይገባዋል፡፡ “የተጀመረው የተስፋ ጭላጭል እንዳይጠፋ ሁላችንም እንደሙያችን፣ እንደችሎታችንና እንደአቅማችን የድርሻችንን በመወጣት ለዜጎች እኩልነትና የህግ የበላይነት መታገል ይኖርብናል'' ብላለች፡፡ “በሀገሪቱ ከዳር እስከ ዳር በተቀጣጠለው ለውጥ የሰው ህይወት አልፏል፣ ታስረው ተሰቃይተዋል” ያለችው አለምጸሃይ፤ ለለውጡ ልጆቻችሁን ለገበራችሁ እናቶች ታላቅ አክብሮት አለኝ ስትል ተናግራለች፡፡ የልኡካን ቡድኑ አባል አርቲስት አበበ በለው በበኩሉ “ይህ ዛሬ የቆምኩበት መሬት የሚገባው ለእኔ ሳይሆን ለዚህ እንድንበቃ ለታገሉ ወገኖች ነው'' ብሏል፡፡ “ባሳለፍኩዋቸው የስደት አመታት ኢትዮጵያን ለአፍታም ቢሆን ከውስጤ አውጥቻት አላቅም'' ያለው ደግሞ አርቲስት ዳዊት ተገኘ ነው፡፡ ምንም እንኳን በውጪ የምንገኘው ኢትዮጵያውያን ዛሬ ለተገኘው ለውጥ የበኩላችን ትግል ብናደርግም የህይወት መስዋእትነት ጭምር በመክፈል ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሹ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ገልጿል፡፡ ለልኡካን ቡድኑ አቀባበል ያደረጉት የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ እርዚቅ ኢሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አሁን ለተጀመረው ለውጥ አስተዋጽኦ ካበረከቱት መካከል በውጪ የሚገኙ አርቲስቶች፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሀገሪቱን የፖለቲካ ለውጥ ከትጥቅ ትግል ወጥቶ በዘመናዊ አስተሳሰብና የሃሳብ የበላይነት ትግል ስልት እንዲተካ በማድረግ በኩል በውጪ የሚኖሩ አርቲስቶች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ያደረጉት ተሳትፎ ትልቅ ስፍራ እንደሚሰጠው አስታውቀዋል፡፡ የጎንደር ከተማ ወጣቶችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የከተማው አመራሮች ለአርቲስት ዓለምፀሐይ ወዳጆና የስጋ አጋሮቿ ከከተማው መግቢያ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡