ቀጥታ፡

በሰርቪያ ቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በአንደኝነት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ቡድን ነገ አቀባበል ይደርገለታል

 አዲስ አበባ መጋቢት 13/2014 /ኢዜአ/ በሰርቪያ ቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በአንደኝነት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ነገ ማለዳ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግለት የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የልዑካን ቡድኑን አቀባበል በተመለከተ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በሰርቢያ ቤልግሬድ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያን ቀዳሚ ደረጃ እንድትይዝ ያስቻሉ አትሌቶችና የልዑካን ቡድኑ ነገ ማለዳ አዲስ አበባ ይገባሉ።

በመሆኑም በቤልግሬዱ ውድድር ተሳታፊዎች ቁጥራቸው አነስተኛ ቢሆነም ያስመዘገቡት ውጤት ግን እጅጉን የሚያኮራ በመሆኑ ለአትሌቶችና ልዑካን ቡድኑ ምስጋና እና ክብር መስጠት እንደሚገባ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን በዓለም የአትሌቲክስ ውድድር መድረክ ያኮራውና ስሟን ከፍ አድርጎ ያስጠራው ይህ ልኡክ በነገው እለት ደማቅ አቀባበል ይጠብቀዋል ብለዋል።

ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት የክብር አቀባበል የሚደረግላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ አትሌቶቻችን ያስመዘገቡት ውጤት መላው ኢትዮጵያዊንን ያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም እነዚህን ጀግኖች ከአየር መንገድ ጀምሮ እስከ ሸራተን አዲስ ሆቴል በደማቅ ሁኔታ ልንቀባለቸው ይገባል ብለዋል።

በሸራተን አዲስ ሆቴል ምስጋና እና ሽልማቱ ተከናውኖ የእለቱ መርሃ ግብር የሚጠናቀቅ ይሆናል።

በቤልግሬድ 2022 በ18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ ሶስት ብር፤ በሁለት ነሐስ በድምሩ 9 ሜዳሊያዎች ኢትዮጵያ ከዓለም አንደኛ ሆና ማጠናቀቋ ይታወሳል።

በውድድሩ አሜሪካ ሁለተኛ ፣ ቤልጂየም ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በቤልግሬድ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከ137 አገራት የተወጣጡ 680 አትሌቶች ተሳትፈዋል። ቀጣዩ 19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.አ.አ በ2023 በቻይና ናንጂንግ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም