የክልሉ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ ባህላዊ እርቅና እሴት ለማጎልበት በቁርጠኛነት እየሰራ ነው - የኦሮሚያ ከልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ ባህላዊ እርቅና እሴት ለማጎልበት በቁርጠኛነት እየሰራ ነው - የኦሮሚያ ከልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት
አዳማ ፤ መጋቢት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሞን ህዝብ ባህላዊ የእርቅ ስርዓት፣ እሴትና ማንነትን ለማጎልበት መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የአሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አረጋገጡ።
"በከረዩ አባገዳዎች ግድያ ትልቅ ስብራት የፈጠረብን ነው፤ ከህግ አንጻር እርምጃ ይወሰዳልም" ብለዋል።
በከረዩ የሚችሌ አባገዳዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ በስህተት መሆኑን ከመንግሥት ጋር መግባባት በመድረስ በኦሮሞ የዕርቅ ሥነ-ሥርዓት ባህል መጠናቀቁን የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በአዳማ አባገዳ አዳራሽ በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት፤ መንግስት የኦሮሞን ህዝብ ባህላዊ እርቅ፣ እሴትና ማንነት ለማጎልበት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የከረዩ አባገዳዎች ላይ የተፈፀመው ድርጊት ትልቅ ስብራት የፈጠረብንና በህዝብ ማንነት ላይ የተቃጣ አደጋ ነው ብለዋል።
ሆኖም በወቅቱ በተፈጸመው ወንጀል እጃቸው ያለበትን አካላት መንግስት በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ ማድረጉንም አመልክተዋል።
የክልሉ መንግስት ከህግ አንፃር የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዳሉ ሆኖ የተፈጠረውን ቅራኔ ለመፍታት በኦሮሞ ባህላዊ እሴትና የገዳ ስርዓት መሰረት መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል።
የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ፀሓፊ የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላ በሰጡት መግለጫ፤ በከረዩ ሚችሌ አባገዳዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ በስህተት መሆኑን ከመንግሥት ጋር ከመግባባት በመድረስ በኦሮሞ የዕርቅ ሥነሥርዓት ባህል መጠናቀቁን አስታወቀዋል።
በወቅቱ የተወሰዱ ንብረትና ገንዘብ መመለሱን የገለጹት አባገዳው፤ የተፈጠረው ቅራኔ በኦሮሞ ባህል በእርቅ እንዲያልቅ የመንግስትና የከረዩ ፍላጎት መሆኑ ታምኖበት ነው ሥርዓቱ የተካሄደው ብለዋል።
የሜጫ አባገዳ ወርቅነህ ተሬሳ በበኩላቸው፤ በወቅቱ ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ስለነበረችና በአካባቢው የፀጥታ ችግር በመኖሩ በደረሰ የተሳሳተ መረጃ ግድያው መፈጸሙን ከመንግሥት ጋር ተማምነናል ነው ያሉት።
በዚህም የኦሮሞ አባገዳዎች ከ8ቱ አርዳ ጂላ በህብረቱ አማካይኝነት ተገናኝተው እውነታውን ወደ ማፈላለግ በመግባት አሁን ጉዳዩን አጣርተው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።አውቆም ይሁን ያለማወቅ ስህተቱን የፈፀሙ አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑም ተጠቁሟል።
ጉዳዩ በኦሮሞ ህዝብ የጉማ ሂደት እንዲጠናቀቅና ዕርቅ እንዲወርድ የከረዩ ኦሮሞ ማህበረሰብ ፍላጎት መሆኑን ጭምር በመግባባት ጉዳዩ በህብረቱ በኩል እንዲያልቅ መደረጉን ያረጋገጡት ደግሞ የአርፈን ቀሎ አባገዳ ሻሚል አህመዶ ናቸው።
የሲኮ መንዶ አባገዳ አሊይ ሙሐመድ ሱሩር በበኩላቸው፤ የከረዩ አባገዳዎች አባላትን ያቀፈና ከሰፊው የከረዩ ማህበረሰብ ከተወከሉ ጋር በጉዳዩ ላይ የጋራ መግባባትና ስምምነት ላይ በመድረስ እርቀ ሰላም እንዲወርድ አድርገናል ነው ያሉት።
አሁን በኦሮሞ የጉማ ስርዓት ለከረዩ አባገዳዎች ተጎጂ ቤተሰብ ጉማ(የደም ካሳ) እንዲከፈል መወሰኑንም አመልክተዋል።የጉጂ አባ ገዳ ሚደጋ ዴንጌ ፤ የኦሮሞ ህዝብ ለዘመናት በሚተዳደርበት የገዳ ስርዓት የእርቅ እሴት መሰረት ጉዳዩን መጨረሳቸውን ነው ያስታወቁት።
የከረዩ አባገዳ ተወካይ አባገዳ ዑመር ሮባ ፤ በወቅቱ ጉዳት ከደረሰባቸው የሚችሌ አባገዳዎች የተወሰደባቸው ገንዘብና ንብረት ተመልሷል፤ የኦሮሞ አባገዳዎችና መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ላሳዩት ቁርጠኝነት እናመስግናለን ብለዋል።
የከረዩ ማህበረሰብ የሀገር ሽማግሌ አቶ ፎቶ ቦሩ ሐዋስ በበኩላቸው ፤ የኦሮሞ ህዝብና አባገዳዎቻችንን ልናመሰግናቸው ይገባል ብለዋል ።
የኦሮሞ ህዝብ የደረሰብንን የልብ ስብራት ለመጠገንና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ የተባበረ እና የሰራ ሁሉ እናመሰግናለን፤ ጉዳያችን በዕርቅ መጠናቀቁም አስደስቶኛል ነው ያሉት።