የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ተሸላሚ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ተሸላሚ ሆነ
አዲስ አበባ ነሃሴ 29/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃዎች የአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ተሸላሚ ሆነ። ሽልማቱን ያገኘው ከዓለም አቀፉ የኤሌክትሮኒክ ጎዞ ባለስልጣን (ኢ ቲ ኤ) መሆኑን አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስታውቋል። 'ኢ ቲ ኤ' ገልተኛ የሆነና እ.አ.አ በ2015 የወጣው 14001 አለም አቀፍ ደረጃ ማዕከል አድርጎ የአካባቢ ጥበቃ አስተዳደርን ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማትን የሚለይና የሚሸልም ተቋም ነው። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የተሰጠው ሽልማት ለአካባቢ ዘላቂ ልማትና አለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ደረጃዎችን መከተላችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል። አየር መንገዱ በመሬት ላይም ይሁን በአየር ላይ ለስነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ ምርቶችና አሰራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንም ነው የገለፁት። በተጨማሪም የአካባቢ ጥበቃን የተከተለ አገልግሎት ለመስጠት በተያዘው የ2025፣ የ15 ዓመቱን ስትራቴጂያዊ እቅድ ለማሳካት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት አዳዲስ ነዳጅ ቆጣቢ አውሮፕላኖች መግዛቱን ተናግረዋል። አየር መንገዱ በሁሉም የስራ ዘርፎች የአካባቢ ጥበቃ አሰራርን ተግባራዊ ማድረጉም ነው የተገለፀው።