በህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የተከሰሱ ግለሰቦች በእስራትና ገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር የተከሰሱ ግለሰቦች በእስራትና ገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

ፍቼ፤ መጋቢት 13/2ዐ14 (ኢዜአ) በህገወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ ዝውውር የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች እስከ ስድስት ዓመት እስራትና የገንዘብ ቅጣት የተወሰነባቸው መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡
ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ላይ እንደተመለከተው፤ በዞኑ ደገም ወረዳ አሊዶሮ ከተማ ቀበሌ ዐ1 ነዋሪ የሆነው አያና በንቲ መስከረም 28 ቀን 2ዐ14 ዓ.ም የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-47161 አዲስ አበባ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ ላይ በጫነው ከሰል ውስጥ 3ሺ 23ዐ የክላሽንኮቭ ጥይቶችን ደብቆ ከጐጃም ወደ አዲስ አበባ ሲያጓጉዝ በፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውሏል።
የጦር መሣሪያ ፍቃድና ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ ወንጀል ተከሶ ድርጊቱንም ማስተባበልና መከላከል እንዳልቻለ የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ መርጊያ ጣሰው ገልጸዋል።
የተከሳሹ ድርጊት በአቃቤ ህግ ማስረጃ በመረጋገጡ ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት በስድስት ዓመት እስራትና አስር ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የተላለፈበት መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ሌላ በዞኑ ወረ ጃርሶ ወረዳ የቀሬ ጐሃ ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ተከሳሽ ስዩም በቀለ የጦር መሣሪያ በመኖሪያ ቤቱ ሸሽጐ በመገኘቱ በአምስት ዓመት ከስድስት ወርና በሁለት ሺህ ብር እንዲቀጣ መወሰኑም ገልጸዋል፡፡
ግለሰቡ ህዳር ዐ2 ቀን 2ዐ14ዓ.ም በፍርድ ቤት ማዘዣ የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ፍተሻ በመኖሪያ ቤቱ 43 የክላሽንኮቭ ጥይቶች የተገኙበት መሆኑን በማስረጃ በማረጋገጥ የቅጣት ውሳኔው እንደተላለፈበት ነው ዳኛው ያመለከቱት፡፡