ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እጇን ለመጠምዘዝ የሚደረጉ ሙከራዎችን አትቀበልም፤ የሉዓላዊነታችን ጉዳይም ለድርድር አይቀርብም

መጋቢት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ኢትዮጵያ እጇን ለመጠምዘዝ የሚደረጉ ሙከራዎችን አትቀበልም፤ የሉዓላዊነታችን ጉዳይም ለድርድር አይቀርብም” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

‘ኤች አር 6600' እና 'ኤስ.3199' ረቂቅ ሕጎች ዳያስፖራው ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ለማቋረጥና ለአገሩ ሉዓላዊነት መጠበቅ ሲያደርግ የነበረውን ትግል ለማጥፋት የተዘጋጁ ረቂቅ ሕጎች ናቸውም ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ መሪዎችና ተወካዮች ጋር የበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።

May be an image of 16 people and text

በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት ፣በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) የጋራ ድጋፍ የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’ በሚል ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ በኮንግረሱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ(ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው ‘ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2021’ ወይም ‘ኤስ.3199’ በአሜሪካ ሴናተር ሮበርት ሜኔንዴዝ(ኒው ጀርዚ) ዋና አርቃቂነት፣በሴናተር ጀምስ ሪስች(ኢዳሆ)፣በሴናተር ክሪስ ኩንስ(ዴልዌር) እና በሴናተር ቶም ቲሊስ(ኖርዝ ካሮላይና) ደጋፊነት የተዘጋጀ ሲሆን፤የሴኔቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ነገ ሊወያያባቸው በአጀንዳነት ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች መካከል አንዱ ነው።

በረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚናገሩ ሰዎች መልዕክቶቻቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዳይተላለፉ እንደሚያደርግና ይህም ዳያስፖራው የአገሩን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያከናውነው ሥራ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ.3199’ ረቂቅ ሕጎች በመላው አለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መጠበቅ ያደረጓቸውን ትግሎችና ያገኟቸውን ስኬቶች ለማጥፋትና ወደ ኋላ ለመመለስ የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ሕጎቹ ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና የደህነት ፍላጎቶችን ለማራመድ በሌሎች መልካም ፈቃድ ላይ ጥገኛ እንድትሆን ለማድረግና ዳያስፖራው ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ለማቋረጥ የተረቀቁ ናቸው” ብለዋል።

ኢትዮጵያና አሜሪካ የረጅም ጊዜና ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መስራት አለባቸው፤ ሆኖም “ኢትዮጵያ እጇን ለመጠምዘዝ የሚደረጉ ሙከራዎችን አትቀበልም፤ የሉዓላዊነታችን ጉዳይም ለድርድር አይቀርብም” ብለዋል አቶ ደመቀ።

ዳያስፖራው በብዙ አቅጣጫዎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶችን በመመከት ላደረገው ጥረት ምስጋና አቅርበው ይሄንኑ ተመሳሳይ ትግል ሁለቱ ረቂቅ ሕጎችን በመቃወምና እንዳይጸድቁ ጥረት በማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበይነ መረብ ውይይታቸው መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እያደረገውያለውን ጥረት አስመልክቶ ለዳያስፖራዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ፍጹም አረጋ በበኩላቸው ሁሉንም አይነት የተግባቦት አማራጮች በመጠቀም ለኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች ረቂቅ ሕጎች በኢትዮጵያ ላይ እንዲሁም በሁለቱ አገራት ግንኙነት ላይ የሚኖረውን አደጋ እንዲረዱ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

May be an image of 1 person and standing

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ዳያስፖራዎች ረቂቅ ሕጎቹ አንድ የፖለቲካ ፓርቲን ወይም ግለሰቦችን ሳይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን መጉዳት ላይ ያተኮሩ በመሆናቸው ህጎቹ እንዳይጸድቁ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ(ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው ‘ኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2021’ ወይም ‘ኤስ.3199’ የተዘጋጀው እ.አ.አ በ2021 ነው።

ረቂቁ የተዘጋጀው የኮንግረስና የሴኔት ኮሚቴዎች በአጭር ጊዜ ሁለቱ ረቂቅ ሕጎች በተመሳሳይ ሰአት ለኮንግረስና ለሴኔት ቀርበው እንዲጸድቁ ለማድረግ ነው።

‘ኤች አር 6600’ በኮንግረስ እንዲሁም ‘ኤስ.3199’ በሴኔት ከጸደቀ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተመርቶ ሲፈርሙበት ሕግ ሆኖ ይወጣል።

በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ረቂቅ ሕጎቹ እንዳይጸድቁ የኮንግረስ አባላትና ሴናተሮችን በማነጋገር እንዲሁም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻዎችን እያደረጉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት አመራሮች በቅርቡ ከአሜሪካ ሴኔት የዴሞክራት መሪ ቻክ ሹመርን በማነጋገር በረቂቅ ሕጎቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱ ከኦክላሃማው ሴናተር ጂም ኢንሆህ ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ለአሜሪካ ኮንግረሰ አፈ-ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ሕጎቹ የሚያደርሱትን ጉዳት የተመለከተ ደብዳቤ አስገብተዋል።

ዳያስፖራው መጋቢት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ‘ኤች አር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በኒው ጀርዚ ሕጉን ባረቀቁት ቶም ማሊኖውስኪ ቢሮ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ረቂቅ ሕጎቹን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መጋቢት 19 ቀን 2019 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ በአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ‘ካፒቶል ሂል’ ፊት ለፊት ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም