ምዕራብ ዕዝ ከህግ ማስከበር እስከ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ ነው --የጦር ኃይሎች ም/ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ - ኢዜአ አማርኛ
ምዕራብ ዕዝ ከህግ ማስከበር እስከ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ ነው --የጦር ኃይሎች ም/ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ

መጋቢት 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ምዕራብ ዕዝ ከህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻው እስከ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ከፍተኛ ድል ያስመዘገበ ነው" ሲሉ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ተናገሩ።
በምዕራብ ዕዝ ለሠራዊቱ አመራሮች የወታደራዊ ሳይንስ እና የአመራር ጥበብ ስልጠና ተሠጥቷል።

ጀነራል አበባው ታደሰ በዚሁ ወቅት ተገኝተው እንደገለጹት ምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት እና አመራሮች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በድል በመወጣት ሀገርን ከብተና ህዝብን ከእልቂት እና ስቃይ መታደግ ችለዋል።
አሸባሪው የህወሃት ቡድን የከፈተውን ጦርነት መቀልበስ የተቻለው ከአመራር እስከ ታችኛው የሠራዊት አባል ባለው የሀገር ፍቅር ስሜት እና ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።
"አመራር ሁለገብ ብቃት እና ልምድ ሲኖረው የሚመራውን ክፍል በስልጠና ያዘጋጃል" ያሉት ጀነራል አበባው ታደሰ ፤ ሠራዊት ሰልጥኖ ለግዳጅ ዝግጁ ሆኖ ሲጠብቅ ውጊያን በአጭር ጊዜ እና ባነስተኛ ኪሳራ ድልን ማስመዝገብ ይቻላል ብለዋል።
"የዕዙ አመራሮች በስልጠና ያገኛችሁትን ወታደራዊ የአመራር ጥበብ ወደ ተግባር በመለወጥ ቀጣይ ለሚሰጣችሁ ግዳጅ ራሳችሁን እና ሠራዊቱን ማዘጋጀት ይኖርባችኋል" ሲሉ መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ስልጠናውን የወሰዱ አመራሮች የምስክር ወረቀት በምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሰለ መሠረት ተበርክቶላቸዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ
