ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የቋንቋ ልማትን የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ  መጋቢት12/2014 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የቋንቋ ልማትን የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር እንደሚገባ የዘርፉ ምሑራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች የሚነገርባት ሕብረ ብሔራዊና ልሳነ-ብዙ አገር ብትሆንም ባለፉት ሥርዓቶች ሁሉም ቋንቋዎች እኩል ድጋፍና እውቅና ሳይሰጣቸው መቆየቱም ይነገራል።

ለትምህርት፣ ለንግድ፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ስርጸት፣ ለባህልና ለስነ-ጽሑፍ እድገት በአጠቃላይ ለዘመናዊ ሥልጣኔ መሸጋገሪያና ለዲፕሎማሲ የቋንቋዎች ጠቀሜታ የላቀ ነው።  

የቋንቋዎችን ልማትና አስተዳደር የሚመራ በህግ እውቅና ያለው ተቋም ባለመኖሩ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በዘፈቀደ የመጠቀም ዝንባሌ ለቅሬታ መነሻ ሲሆን ይስተዋላል።

ከአንድ ዓመት በፊት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያጸደቀው የቋንቋ ፖሊሲ ለቋንቋ የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ቢሆንም፤ ለቋንቋ እድገት የሚሰራ ተቋማዊ አደረጃጀት እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ በርካቶች ይስማማሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልሳን ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሞገስ ይገዙ፤ የኢትዮጵያ ብዝሃ ቋንቋዎች በሚፈለገው ደረጃ ባለመመራታቸው እድገት ሳያስመዘግቡ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

በተለይም ቀደም ባሉት ጊዜያት ያለ በቂ ዝግጅትና ጥናት የሥራና የትምህርት ቋንቋዎች ተግባራዊ መደረጉና በተቋማዊ ሥርዓት ባለመመራቱ  በርካታ ችግሮችን ፈጥሮ ማለፉን ገልጸዋል።

የቋንቋዎችን ብዝሃነት ማስተናገድ ባለመቻልና የቋንቋን ልማት የሚደግፍ በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው አካዳሚ ባለመኖሩ እድገቱን ገድቦት ቆይቷል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ከተቀመጠው የመብት ጉዳይ ባለፈ ዝርዝር ፖሊሲ አለመኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ሞገስ ክልሎችም በመሰላቸው መንገድ እየሰሩ መዝለቃቸውን ጠቅሰዋል።

የቋንቋዎችን ልማት ለማሳደግ የተወሰደው ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት የተሻለ እድገት እንዲኖር መደላድል እየፈጠረ ቢሆንም፤ የቋንቋ ልማትን የሚመራ ተቋማዊ አደረጃጀት ያስፈልጋል ብለዋል።

የተለያዩ ቋንቋዎችን ለሚዲያ ልማት፣ ለትምህርት የማዋሉ እና የቋንቋ ፖሊሲ መዘጋጀቱ በመንግስት የተሰጠውን ትኩረት አመላካች መሆኑን ያሳያል ይላሉ።

የፌዴራል የሥራና የትምህርት ቋንቋዎች እንዲበዙ መደረጉ ዜጎች በቋንቋቸው የመማር፣ የመሥራትና ባህላዊ እሴቶቻቸውን የመጠቀም መብታቸውን መስጠት መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይ ዜጎች የቋንቋ ብዝሃነትን የመቀበል ፍርሃታቸውን ሊያስወግዱና በአገር በቀል እውቀቶቻቸው ችግሮቻቸውን መፍታትና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ለእድገቱ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ሊያጠናክሩ እንደሚገባም መክረዋል።

በዓለም ላይ ልሳነ-ብዙ የሆኑ አገራትና ብዝሃነታቸውን እንዴት እያስተናገዱ እንደሆነ ከህንድ፣ ኢንዶኔዢያና ሌሎች አገራት ተሞክሮ መውሰድ ጠቃሚ መሆኑንም አንስተዋል።

በቅርቡ የጸደቀውን ፖሊሲ ለመተግበር፣ ለአገርና ለህዝቦች የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በመረዳት ለአፈጻጸሙ ሰፊ ጥረትና ትብብርን የሚጠይቅ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ  ሁሉም ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል።

የቋንቋና የስነ-ቃል ምሑሩ ዶክተር አውላቸው ሹምነካ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ የቋንቋ ልማት በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለው።

በተለይ 53 የሚያህሉ ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ወደ ሥራ መግባቱ እንዲሁም ክልሎች ቋንቋቸውን የትምህርት፣ የሥራና የሚዲያ አድርገው መጠቀም መጀመራቸው የእድገቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከአማርኛ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ፣ አፋርኛ፣ ሶማሌኛንና ትግርኛን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ የተጀመረው ጥረትም ኢትዮጵያ ያላትን የቋንቋ ሃብት ሥራ ላይ ለማዋል መጀመሯን ያሳያል ነው ያሉት።

በተጨማሪ የፖሊሲው መጽደቅ በአገሪቱ ያሉ ቋንቋዎችን ሥርዓት ማስያዝና በህገ-መንግስቱ የተሰጣቸውን መብት በአግባቡ ለመተግበር ያግዛል።

እንደ ዶክተር አውላቸው  ገለጻ፤ የቋንቋዎች እድገት የህብረተሰቡን አብሮነት የሚያጎለበት ሲሆን አገር በቀል እውቀቶችን ተጠቅሞ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያስችላል ብለዋል።

ፖሊሲውን ለመተግበር ደንቦች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን በተሻለ ጥቅም ላይ ለማዋል ሁሉም በጋራና ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት ብለዋል።

የፖሊሲው ዋና ዓላማ የቋንቋ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ መተግበር፣ ልሳነ-ብዙነትን ማበረታታት፣ በቋንቋ ዙሪያ የሚያጋጠሙ ችግሮችን መፍታትና የቋንቋ ልማትን ሥርዓት ማስያዝ መሆኑን ፖሊሲው ያስቀምጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም