የኢትዮጵያ ህዝብ የአገራዊ ምክክሩን ጠቀሜታ ተገንዝቦ በንቃት እንዲሳተፍ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ህዝብ የአገራዊ ምክክሩን ጠቀሜታ ተገንዝቦ በንቃት እንዲሳተፍ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነው
መጋቢት 12/2014(ኢዜአ) ''የኢትዮጵያ ህዝብ የአገራዊ ምክክሩን ጠቀሜታ ተገንዝቦ በንቃት መሳተፍ እንዲችል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን'' ሲሉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ መሪዎች ገለጹ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ አገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።
የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ሰለሞን፤ አገራዊ ምክክሩ አስተማማኝ ሰላምና ዘላቂ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ አገር ጠንካራ አገረ መንግስት እንዲመሰረት፣ የታቀዱ የልማት ግቦች እውን እንዲሆኑም ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይህም በመሆኑ ህዝቡም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ሊጠቀምበት ይገባልም ብለዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰጠኝ አቦሃይ በበኩላቸው፤ አገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያዊያንን ቁርሾ ውስጥ እንዲገቡ ያደረጉ ጉዳዮች ወደ መድረክ በማምጣት እልባት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
የተሻለች፣ ዜጎቿ የሚግባቡባትና የሚተባበሩባት አገር እንድትፈጠር አገራዊ ምክክሩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል።
ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ እንዲሁ አገራዊ ምክክሩ የተሻለች አገር ለመፍጠር ያግዛል ይላሉ።
''የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት ታላቅ አበርክቶ አለው'' ያሉት ኃላፊው ለህዝቡ ጠቀሜታውን በማስገንዘብ የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ ህዝቡ የአገራዊ ምክክሩን ጠቀሜታ ተገንዝቦ በንቃት እንዲሳተፍ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
ስለ ምክክሩ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ለህዝቡ በማስረዳት ተመሳሳይ ግንዛቤ ያለው ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ አካታች የሆነ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል።