የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ ለተፈናቃዮች 723 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ ለተፈናቃዮች 723 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ
ሰቆጣ (ኢዜአ) መጋቢት 11/2014---የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች 723 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ወሌ ለኢዜአ እንደገለጹት ድጋፉ ''ለወገን ደራሽ ወገን ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ ከህዝቡ የተሰባሰበ ነው።
አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች ህዝቡ ያደረገው የምግብ እህል ድጋፍ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላው መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፉ ጤፍ፣ በቆሎ፣ ሽንብራና ሌሎች የምግብ እህሎች እንዲሁም የገብስ ቆሎ፣ ድርቆሽና ዳቦ ቆሎ ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ የአዊ ብሔረሰብ ህዝብ የመረዳዳት ባህሉን በማጎልበት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደስታዬ ጌታሁን በበኩላቸው፣ በብሔረሰብ አስተዳደሩ የተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ለተፈናቀሉ ወገኖች በሚያደርገው ድጋፍ ብቻ ችግሩን ማቃለል ባለመቻሉ የህዝቡና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
"የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ በማድረግ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን በተግባር አሳይቷል" ብለዋል።
ዛሬ የተደረገው የእህል ድጋፍ በቀጥታ ለተፈናቃይ ወገኖች እንደሚከፋፈል ገልጸው፤ ድጋፉ የተፈናቃዮችን ወቅታዊ ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ህዝብ ያለውን ወቅታዊ ችግር ተረድቶ አጋርነቱን ለማሳየት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ለመቅረፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከ61 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሰቆጣ፣ ፅፅቃ እና ወለህ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።