ቀጥታ፡

አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አሸነፈ

መጋቢት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ3 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ በማሸነፍ ለኢትዮጵያ ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ።

አትሌት ለሜቻ ግርማ ሁለተኛ ወጥቷል።

በሰርቢያ ቤልግሬድ እየተካሄደ ያለው 18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የመጨረሻ ቀን ውድድሮች ዛሬ እየተካሄዱ ነው።

በ 3 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ሰለሞን ባረጋ 7 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ከ38 ማይክሮ ሰከንድ አሸናፊ በመሆን ለኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ሶስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።

ሌላኛው አትሌት ለሜቻ ግርማ 7 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ ከ63 ማይክሮ ሰከንድ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝቷል።

የዩናይትድ ኪንግደሙ ማርክ ስኮት 7 ደቂቃ ከ42 ሰኮንድ ከ2 ማይክሮ ሰከንድ ሶስተኛ ወጥቷል።

ውጤቱን ተከትሎ የሻምፒዮናውን የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በሶስት ወርቅ በሁለት ብር፤ ሁለት ነሐስ በድምሩ ሰባት ሜዳሊያዎችን በማግኘት በአንደኝነት መምራቷን ቀጥላለች።

በሻምፒዮናው የኢትዮጵያ አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ ።

ከምሽቱ 2 ሰአት ከ5 ደቂቃ ላይ በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ሃብታም አለሙና አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

ከምሽቱ 2 ሰአት ከ30 ደቂቃ በ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች አትሌት ሳሙኤል ተፈራና አትሌት ታደሰ ለሚ ይሳተፋሉ።

ትናንት ማምሻውን በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት መውጣታቸው የሚታወስ ነው።

18ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም