የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ የማድረግ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል

375

መጋቢት 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንዲሚገባ ተመለከተ።


ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አካሂዷል።


በውይይቱም ላይ የተለያዩ አካል ጉዳተኞች ማኅበራት ተወካዮች፣ የሆቴሎች ማኅበርና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።


የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት ሚናን በዝርዝር ያካተተ ሰነድም ይፋ ተደርጓል።


የአካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማኅበራት ፌደሬሽን ተወካይ አቶ ማቱሳላ መና እንደተናገሩት፤ ከቱሪዝም ልማት ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ማድረግ ላይ ግን ክፍተቶች ይስተዋላሉ።


በተለይም በዘርፉ አስፈላጊ መረጃዎችን ለአካል ጉዳተኞች በበቂ መጠን መስጠት እንደሚገባ ያመለከቱት ተወካዩ በዘርፉ አካል ጉዳተኛ ሙያተኞችን ማፍራት በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።


በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት አቶ ይስፋልኝ ኃብቴ በበኩላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያለው አካል ጉዳተኛ መኖሩን ለአብነት የጠቀሱ ሲሆን ይህንን ያላካተተ የቱሪዝም ልማት ግቡን ሊመታ አይችልም ብለዋል።


የአካል ጉዳተኛ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገብረ-ማሪያም በበኩሉ የቱሪስት ማዳራሻ ሥፍራዎችን ምቹ ለማድረግ ካደጉት አገራት ተሞክሮ መቅሰም እንደሚገባ ተናግሯል።


ከቱሪዝም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሆቴሎች፣ሪዞርቶችም በአብዛኛው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አይደሉም፤ ሊሰራበት ይገባል ሲል ነው አጽንኦት የሰጠው።


አካል ጉዳተኞች የቱሪዝም ቦታዎችን በቀላሉ እንዲጎበኙ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ቁልፍ ጉዳይ ነው ያለው ጋዜጠኛ ተስፋዬ ይህም ሊጤን ይገባል ብሏል።


ከኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ብሔራዊ ማኅበር የተገኙት አቶ ገብሬ ተሾመ እንደተናገሩት፤ አካል ጉዳተኞች ሳይቸገሩ እንዲጎበኙ መንገድን ጨምሮ መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ሊሰራ ይገባል።


በተለይም እኛ አይነ ሥውራን ብዙነገር በመዳሰስ ነው የምንጎበኘው ያሉት አቶ ገብሬ የሚጎበኘው ዓይነት ቅርስ ምስለኔ ተዘጋጅቶ ዓይነስውሩ እየዳሰሰ እንዲጎበኝ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።


በቱሪዝም ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ ሙሉነህ ማቲዎስ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች የጉብኝት ባህላቸውን የሚያሳድግ ሰነድ ተዘጋጅቷል።


ሰነዱ የተለያዩ ማበረታቻዎችን የያዘ ሲሆን አካል ጉዳተኞች በሚጎበኙበት ቦታ በቅናሽ እንዲስተናገዱ ማድረግ አንዱ መሆኑን አብራርተዋል።


ከዚህ ባሻገርም ሰነዱ ትራንስፖርት፣ ግንባታ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኅበራት በቅንጅት መሥራት የሚችሉበት አሰራር የተካተተበት መሆኑም አስረድተዋል።


ሰነዱን መነሻ በማድረግ አካል ጉዳተኞችን በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎ ለማጎልበት ከባለድርሻ አካላት ጋር የስምምነት ፊርማ በማድረግ ወደ ሥራ እንደሚገባ አረጋግጠዋል።


ከዓይነ ስውራን ጋር በታያያዘ የሚነሳውን ጥያቄ ለመፍታት ዓይነ ስውራን እንዴት መጎብኘት ይችላሉ የሚለውን ዝርዝር መረጃ የያዘ መጽሃፍ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም