የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለአገራዊ ራዕይ መሳካትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር በትኩረት ይሰራል

መጋቢት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአገራዊ ራዕይ መሳካትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቀጣይ ለህዝብ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ግንዛቤ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩም የኮሙኒኬሽን አካላት በህዝብ መካከል ያለውን መስተጋብር በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ሊሰሩ እንደሚገባ ተመላክቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሀላፊ ሚኒስትር ዶክትር ለገሰ ቱሉ፤ ተቋሙ ከተመሰረተ አምስት ወራት ማስቆጠሩን አስታውሰው፤ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ምክንያት ከስሩ ከመገኙ መዋቅሮች ጋር በሚገባው ልክ ግንኙነት እንዳልነበረው አንስተዋል።

አሁን ተቋሙ ያዘጋጃቸውን መመሪያዎች እና አጠቃላይ አሰራሮችን ከስሩ ከሚገኙ አካላት ጋር በመወያየት ለስኬታማነቱ የሚሰሩ መሆኑም ጠቅሰዋል።

በውይይቱም የኮሙኒኬሽን ስራዎች የሚከተሉት መርሆዎችና አሰራሮች እንዲሁም የመረጃ ስርጭቱ "እንዴት ተደርጎ መቀናጀት አለበት" በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡

ይህም የመረጃ ስርዓቱ የተሳለጠ እንዲሆን በማድረግ ለዕቅዶች ስኬት የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የኮሙኒኬሽን አካላት ከሚዲያ ተቋማት ጋር ይበልጥ ተቀራርበው በጋራ እንዲሰሩ ማስቻልም የመድረኩ ሌላኛው ዓላማ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር፣ ብዝሃነት በተሻለ መልኩ እንዲጎለብት ተቋሙ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

ለአገራዊ ራዕይ መሳካትና በህዝቦች መካከል ያለው የመረዳዳት፣ የመከባበር ባህል እንዲጠናከር ለማድረግም ተቋሙ ትኩርት አድረጎ ይሰራልም ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የአገሪቱን ዋና ዋና ወቅታዊ መረጃዎችን ማድረስ ላይ ትኩርት ተደርጎ የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የደቡብ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት አንድ አገር እንዲያድግና እንዲቀየር ሚዲያና ኮሙኒኬሽን በእጅጉ ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

ለአገር ብልጽግና መረጋገጥም "የህዝቦች አስተሳሰብ ሊለወጥ ግድ ነው" ያሉት ሃላፊዎቹ ዜጎች የተሻለ እሳቤ ኖሯዋቸው ለአገር እንዲሰሩም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በህዝብ እና በመንግሥት መካከል መልካም ግንኙነት እንዲዳብር የኮሙኒኬሽን አካሉ አተኩሮ ሊሰራበት እንደሚገባም መክረዋል፡፡

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የስራ ሃላፊዎችም የመገናኛ ብዙሃን እና የኮሙኒኬሽን አካላት ግብ በመረጃ የበለጸገ ማህበረሰብ መፍጠር በመሆኑ ተባብረው መስራት ግድ ይላል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ወደ ተግባር መሸጋገሩ ሚዲያዎች መረጃን በዘላቂነት እና ወጥ በሆነ መልኩ እንደያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ሃላፊዎች፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሮች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም