ቀጥታ፡

በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ የህክምና ባለሙያዎች ለነበራቸው የላቀ ሚና ተመሰገኑ

መጋቢት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)  በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ የህክምና ባለሙያዎች ለነበራቸው የላቀ ሚና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ምስጋና አቀረቡ።

በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ለተሳተፉ የህክምና ባለሙያዎች የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት የእውቅና መርሐ ግብር ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በህግ ማስከበርና በህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ የህክምና ባለሙያዎች ሚና የላቀ እንደነበር አስታውሰዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አገር ለማዳን በዱር በገደሉ በሚዋደቅበት ወቅት የህክምና ባለሙያዎችና የዘርፉ ሃላፊዎችም ከሰራዊቱ ጎን እንደነበሩ ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት የህክምና ባለሙያዎች የሰራዊቱ አባላትን በማከምና በመንከባከብ የነበራቸው ሚና በምሳሌነት የሚጠቀስ የጀግንነት ተግባር መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጠቅሰዋል።

የህክምና ዘርፉ ከመከላከያ ሰራዊት የህክምና ተቋማት ጋር የነበራቸው ቅንጅት የሚያኮራ እንደነበር አስታውሰው አጠቃላይ የህክምና ባለሙያዎች ለነበራቸው የላቀ ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች በጦር ሜዳ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም አክሞ ሰው ማዳን እንደሚቻል በተግባር አሳይታችኋል በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም