ቀጥታ፡

በሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ የ313 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

መጋቢት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) "አግማስ ኢትዮጵያ" የተሰኘ በጎ አድራጎት ድርጅት በሰብአዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ የ313 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

"አግማስ ኢትዮጵያ " ይህንን የሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ዕቅድ ይፋ ያደረገው ዛሬ የድርጅቱን ይፋዊ ምስረታ ሲያካሂድ ነው።

የአግማስ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱሰላም ሽፋው፤ ድርጅቱ በሃብት ልማትና ሰላም ላይ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በተወሰኑ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት፣ መፈናቀል እና ድርቅ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ሥራ ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ዛሬ ይፋ የተደረገው የ313 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክትም በጦርነት እና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግና መልሶ ለማቋቋም እንደሚውል ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ለቀጣይ አምስት አመታት ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ገልጸው፤ በትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም የውሃ አቅርቦት ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በትምህርት፣ በጤና፣ በማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በወጣቶች እና በሕጻናት፣ በግብርና እና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ መርሃግብሮችን ቀርጾ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በጦርነትና ድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የበኩሉን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

አግማስ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ሕጋዊ ዕውቅና ተሰጥቶት ከጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም