ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የድርቅ ተጋላጭነትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው

አዳማ ፤ መጋቢት 10/2014(ኢዜአ) የተለያዩ የልማት አማራጮችን በመጠቀም በክልሉ የድርቅ ተጋላጭነትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ የአደጋ ስጋት ቅነሳና የልማት ተነሺዎች ኮሚሽን አስታወቀ ።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ድርቁ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የእንስሳት መኖ በመግዛት በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

የኦሮሚያ የአደጋ ስጋት ቅነሳና የልማት ተነሺዎች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተፈሪ በየነ ለኢዜአ እንደተናገሩት በድርቁ ምክንያት በክልሉ  ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ  ህዝብ ድጋፍ ይፈልጋል።

ይህም ሆኖ መንግስትና ሌላም ህብረተሰብ ለተጎጂዎች የምግብና የቁሳቁስ  ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

እንዲሁም በክልሉ ዘጠኝ ዞኖች ድርቁ ባስከተለው ችግር እየተጎዳ ያለውን የእንስሳት ሀብት ለመታደግ የክልሉ መንግስት ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ዘርፈ ብዙ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት ጨምሮ የተለያዩ የልማት አማራጮችን በመጠቀም  የድርቅ ተጋላጭነትን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቦረና፣ጉጂ ፣ምስራቅ ባሌና በሌሎች የክልሉ ዞኖች እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይ ግድቦቹን ፈጥነን በማጠናቀቅ ለሰውና ለእንስሳት መጠጥ፣ለመኖና ሰብል ልማት ለማዋል ግብ አስቀምጠን እየሰራን ነው ብለዋል።

ችግሩን በአጭርና ረጅም ጊዜ ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የመኖ አቅርቦት፣የእንስሳትና የሰው የመጠጥ ውሃ በቦቴ ከማመላለስ ባለፈ መካከለኛና ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ባለድርሻ አካላትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

በእስካሁኑ ሂደት በክልሉ በድርቁ ምክንያት በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው፤ ድርቁ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ የእንስሳት መኖ በመግዛት በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በድርቁ ምክንያት የእንስሳት በሽታዎች ጭምር እየተከሰቱ ነው ያሉት ዶክተር ፍቅሩ፤ ሚኒስቴሩ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የእንስሳት ክትባትና መድሃኒት ገዝቶ ወደ የክልሎቹ እያጓጓዘ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፈንታሌና ቦሶት  ጨምሮ  በዞኑ ቆላማ ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ ለመቋቋምና የእንስሳት ሀብቱን ለመታደግ ርብርብ እያደረግን ነው ያሉት ደግሞ የምስራቅ ሸዋ ዞን የአደጋ ስጋት አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽሕፈት ቤት ተወካይ  አቶ ተማም ሁሴን ናቸው።

መንግስት፣መንግስታዊ ያልሆኑ ለጋሾች፣ተቋማትና ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከምግብ እህልና መኖን ጀምሮ የተለያዩ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም