በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ዜጋ ከግላዊ ፍላጎት በመላቀቅ ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል- የጋሞ አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ዜጋ ከግላዊ ፍላጎት በመላቀቅ ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል- የጋሞ አባቶች
አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 10/2014 (ኢዜአ) ለሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ሁሉም ዜጋ በሀገራዊ ምክክሩ ከግል ፍላጎት በመላቀቅ ገንቢ ሚና ሊጫወት ይገባል ሲሉ የጋሞ የባህል አባቶች ተናገሩ ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጋሞ ህዝብ የባህል አባት አቶ መንግስቱ ደምሴ በሰጡት አስተያየት፤ ሁላችንም ወደኋላ ከሚጎትቱን የጥርጣሬና ጥላቻ መንፈስ በመላቀቅ በጋራ ከምንፈልገው ደረጃ ለመድረስ በይቅርባይነትና አብሮነት የምንጓዝበትን መንገድ መገንባት ይገባናል ብለዋል።
ስንተማመን ኢትዮጵያን በጋራ አልምተን መጠቀም እንችላለን ያሉት አቶ መንግስቱ፤ ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ለዚህ እሳቤ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
ምክክሩ ኢትዮጵያዊያን እርስ በርሳችን ብሎም ከፈጣሪያችን ጋር የምንታርቅበት፤ከግል ይልቅ በጋራ የማሸነፍን ሥነ-ልቦና የምንገነባበት ሀገራዊ ኩነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህን ታላቅ ዕድል በአግባቡ መጠቀም እንድንችልና ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ከግለኝነት አስተሳሰብ ተላቀን ኢትዮጵያውያን አርቀን በማሰብ በቅንነት ልንሳተፍ ይገባል ነው ያሉት።
በእኛ ዘመን ያስተናገድነው ወንድምን ከወንድሙ ደም የሚያቃባ የማይጠቅም የጥላቻ አጀንዳ ማብቂያው ምዕራፍ አሁን ሊሆን ይገባል ሲሉ አመላከተዋል።
"ተጎድቶም ቢሆን ለዘላቂ ሠላምና አብሮነት ሲባል በይቅርታ ማለፍ የጋሞ ህዝብ በባህሉ ያዳበረው እሴት ነው" ብለዋል።
ተመሳሳይ እሴቶች በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ በመሆናቸው ከማይጠቅሙን ከፋፋይ አስተሳሰቦች ይልቅ አባቶቻችን በራሳችን የዘረጉልንን ባህላዊ ስርዓት ተጠቅመን ዘላቂ ሠላምና ወንድማማችነትን መገንባት ያስፈልገና ሲሉ አቶ መንግስቱ አብራርተዋል።
"በምክክር መድረኩ ያልተስማማንባቸው ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን በሂደት እየፈታን ለመሄድ መሰረት ጥለን ማለፍ አለብን" ብለዋል።
ሀገራችን አሁን ከምትገኝበት ፈተና ወጥታ ፊቷን ወደ አንድነትና ልማት ማዞር እንድትችል የምክክር መድረኩ ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ ሌላው የሀገር ሽማግሌ አቶ ተፈራ ኦይቻ ናቸው።
በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ቅንነትንና ሆደ ሰፊነትን ይዞ በመቅረብ ኢትዮጵያን በጋራ ለማልማት የሚያስችል መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ በዚህ ላይ ለሀገራዊ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቆም ብሎ በማሰብ ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትገኝበት ችግር የዳረጓትን ሁኔታዎች በማጤን ከጥላቻና ፍረጃ ርቆ ተደጋግፎ በጋራ ማደግ የሚቻልበትን መደላድል መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የጋሞ ህዝብ ታላላቆችን የሚያከብርበትና እርስ በርስ የመደማመጥ እሴቱ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን አብሮነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳስቻለው ጠቅሰው፤ መደማመጥና መከባበር የሰፈነበት ውይይት ማድረግ ለዘላቂ ሀገራዊ ሠላም እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል ።
ሀገራዊ ምከክሩ በልሂቃን ደረጃ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀርና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በንቃት እንዲሳተፍበት ለማስቻል ከወዲሁ ቅድመ ሁኔታዎች ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅና ኮሚሽኑን የሚመሩ የ11 ኮሚሽነሮች ሹመት በቅርቡ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ ሲሆን ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉን አካታች የሆነ ሠላምና ሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ እንደሚያተኩር ቀደም ብሎ ይፋ ተደርጓል።