የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 10/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሄደ ነው::
በጉባኤው ላይ የአክሲዮን ማህበሩ የውድድርና ሥነ-ሥርዓት ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ወገኔ ዋልተንጉስ፣ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ዙር 'ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ' ጨዋታ ውድድሩን የሚመሩ አንዳንድ ዳኞች በኩል አቅም ማነስ እንደነበረ ገልጸዋል።
አንዳንድ ዋና ዳኞችና ረዳቶች ሊጉን የማይመጥን ውሳኔ ሲሰጡ እንደነበርና የጨዋታ ኮሚሽነሮችም በትክክል ሪፖርት አለማድረግ ችግር መስተዋሉንም አንስተዋል።
በቀጣይ የዳኞች ምደባ ታሳቢ ማድረግ ያለበት የጨዋታ ህግ አተረጓጎም ዙሪያ በቂ እውቀት ያላቸውና የአካል ብቃታቸው ከፍ ያለ ዳኞች ላይ መሆኑንም ገልጿል።
የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ዳኞችን በማብቃት በኩል ብዙ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በመጀመሪያው ዙር የሜዳ ቦታዎች ጥራት ማነስና የመለማመጃ ቦታ ችግር በስፋት ከታዩ ክፍተቶች መካከል መሆኑን አንስተዋል።
አንዳንድ ተጫዋቾች ሰዓት ለመግደል ጨዋታ ማዘግየት መታየቱም በክፍተት ከተነሱት መካከል ናቸው።
በጠንካራ ጎን ደግሞ አስተናጋጅ ከተሞች ለውድድሩ ያደርጉት የነበረው ትጋት ተነስቷል።
የውድድሩ ሁለተኛ አስተናጋጅ በነበረው ድሬደዋ ከተማ የጸጥታ አካላት ሲያደርጉ የነበረው ተግባር ለቀጣይ አስተናጋጅ አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።