የኢትዮጵያ መንግስት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንግስት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንዳለበት በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።
‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም 'ኤችአር 6600' በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ‘ኤችአር 6600’ ኢትዮጵያን ለመጉዳትና ለማዳከም የተዘጋጀ ረቂቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ አሜሪካን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዳታገኝ፣ የመሳሪያ ግዢ እንዳትፈጽም የሚከለክልና ጫና የሚያሳድር መሆኑን ተናግረዋል።
በረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚናገሩ ሰዎች መልዕክቶቻቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዳይተላለፉ እንደሚያደርግና ይህም ዳያስፖራው የአገሩን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያከናውነው ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመልክተዋል።
በጥቅሉ ረቂቅ ሕጉ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ የማስቆም ዓላማ ያለው እንደሆነም የኢትዮ-አሜሪካ የዜጎች ምክር ቤት ተሟጋች (አድቮኬት) አስኳል ተፈሪ እና በቨርጂኒያ የፑሽስታርት ሚዲያ ሪፖርተር ቤቲ ተከስተ የተባሉ ትውልደ ኢትጵያውያኑ ያስረዱት።
በመሆኑም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ዳያስፖራዎች አንድ በመሆን ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ አደጋ ላይ የሚጥለው ሕግ እንዳይጸድቅ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ረቂቅ ሕጉ የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ጥቅም የሚጎዳና የአገራቱን የጋራ ፍላጎት የማያስጠብቅ እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አለመረጋጋት የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ሕጉ ለአሸባሪው ሕወሓት የልብ ልብ የሚሰጥና የኢትዮጵያን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነም ተናግረዋል።
ይኸው ሕግ ከጸደቀ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ በኢትዮጵያና በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።
በአሜሪካ በሚገኙ በሲቪክ ተቋማት በኩል ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ ሆኖ እንዳይጸድቅ የኮንግረስና የሴኔት አባላትን እያነጋገሩና ደብዳቤ እየጻፉ መሆኑንም አክለዋል።
ከኮንግረስ አባላትና ሴናተሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች መልካም ምላሾች እንደተገኙና አሁንም ሕጉ እንዳይጸድቅ የማድረግ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ አግባቢ (ሎቢስት) ለመቅጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው ዳያስፖራዎቹ የገለጹት።
የኢትዮጵያ መንግስትም ወደ አሜሪካ ልዑክ መላክን ጨምሮ ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚኖርበትና ሕጉ በኢትዮጵያ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ከግምት ባስገባ መልኩ ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።
እ.አ.አ በ2022 ዓ.ም በሚካሄደው የአሜሪካ አጋማሽ ዓመት ምርጫ (ሚድ ተርም ኢሌክሽን) ላይ በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ሥራ የሚያከናውኑ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን በድምጹ እንዲቀጣ ዳያስፖራዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የሚሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በኒው ጀርሲ ግዛት መካሄዱ የሚታወስ ነው።
ኤችአር 6600 በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒውዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን (ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) የጋራ ድጋፍ የተዘጋጀው ነው።