ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ከኦክስፋም ኢንተርናሽናል ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ከኦክስፋም ኢንተርናሽናል ዋና ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
መጋቢት 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኦክስፋም ኢንተርናሽናል ዋና ዳይሬክተር ጋብሪኤላ ቡቸርን ጋር ተወያዩ።
በውይይቱ ድርቅ ኮቪድ-19፣ ግጭት እና መፈናቀል በኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ መጣሉ የተነሳ ሲሆን ከኦክስፋም እና ከሌሎች የሰብዓዊ አጋሮች ሁለገብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
አቶ ደመቀ እንዳሉት ፥ በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በድርቅ የተጎዱ እና አፋጣኝ የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ኦክስፋምን ጨምሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ሶማሌ ክልል እና ቦረና እና ደቡብ ኦሞ ዞኖችን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ወደ 23 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፎችን ለማቅረብ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አብራርተው ፥ ህወሓት በአጎራባች ክልሎች እየፈጸመ ያለው የሽብር ተግባር የመንግስትን ጥረት ማደናቀፉ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በመንግስት በኩል እየተወሰዱ ስላሉ አበረታች እርምጃዎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ፥ ይህም መንግስት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ጠቅሰዋል።
አቶ ደመቀ ኦክስፋም በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አድንቀው ፥ ድርጅቱ በሀገሪቱ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉ ቃል ገብተዋል።
የኦክስፋም ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው ፥ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ የሚደርሱ ችግሮች የበርካታ ሰዎች ህይወት ላይ የሚያደርሱትን ተጽዕኖ እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ችግር ለመቅረፍም ድርጅታቸው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም መግለፃቸው ከውጭጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በውይይቱ በኢትዮጵያ የኦክስፋም ዳይሬክተር ፣ በአፍሪካ ቀንድ ፣ ምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ በኦክስፋም የቀጠናው የፕሮግራሞች ኃላፊ እና የአፍሪካ ህብረት የኦክስፋም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተሳትፈዋል።