በቀጣይ አምስት ዓመታት በሁሉም የኢትዮጵያ ወረዳዎች "ጂን ኤክስፐርት" የተሰኘውን የቲቢ መመርመሪያ ማሸን ለማዳረስ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ አምስት ዓመታት በሁሉም የኢትዮጵያ ወረዳዎች "ጂን ኤክስፐርት" የተሰኘውን የቲቢ መመርመሪያ ማሸን ለማዳረስ ይሰራል
መጋቢት 9/2014/ኢዜአ/ በቀጣይ አምስት ዓመታት በሁሉም የኢትዮጵያ ወረዳዎች "ጂን ኤክስፐርት" የተሰኘውን የቲቢ መመርመሪያ ማሸን ለማዳረስ እንደሚሰራ የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
"ማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ኸልዝ" የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት በየዓመቱ መጋቢት 15 ቀን የሚከበረውን የዓለም የቲቢ ቀን ምክንያት በማድረግ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩም ከጤና ሚኒስቴር፣ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች የመጡትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤ የቲቢ በሽታ ሥርጭትን መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ምክትል ዳይሬክተር ታዬ ለታ በዚህን ወቅት የላቦራቶሪ ምርመራ አገልግሎትን ማስፋት የቲቢ በሽታን ለመከላከል ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ 4 ሺህ የሚሆኑ የቲቢ መመርመሪያ ማሽኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
ነገር ግን መድኃኒት የተላመደ የቲቢ በሽታን ለመመርመር የሚያግዘው "ጂን ኤክስፐርት" የተሰኘው መሳሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ 364 ብቻ መኖሩን ገልጸዋል።
በቀጣይም አምስት ዓመታት በሁሉም ወረዳዎች ይህንን መሳሪያ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
የማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ኸልዝ የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ዳንኤል ገመቹ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የቲቢ በሽታን ለመከላከል ብሎም ለማከም ጠንካራ የላቦራቶሪ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ በጥናት መለየቱን አንስተዋል፡፡
በጥናቱ የመረጃ ቅብብሎሽን ማዘመን እና ጥራት ያለው ህክምና በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ማድረግ ተመላክቷል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የቤት ለቤት ግንዛቤ የመፍጠርና የመከላከሉን ሥራ ማጎልበት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡
በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የቲቢና ኤች አይ ቪ ምርምር ዳይሬክቶሬት የቲቢ ላቦራቶሪ ኃላፊ ምስክር አማረ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቲቢ ታማሚ ቁጥር ካለባቸው አገሮች ውስጥ እንደምትመደብ ተናግረዋል፡፡
የበሽታውን ሥርጭት ለመቀነስ በዘርፉ ጥራት ያለውና ተደራሽ የህክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በዓመት በቲቢ በሽታ ይያዛሉ ተብለው ከሚገመቱ 157 ሺህ ሰዎች መካከል 29 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚሄዱ መረጃዎች ያመላክታሉ።